ግለሰቡ ሩጫውን ለማጠናቀቅ ልምምድ ሲያደርግ መሰንበቱን ገልጿል
የለንደን ማራቶን በሚቀጥለው ወር የሚካሄድ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በታዋቂው ውድድር ላይ ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ ናቸው።
በውድድሩ እንግዳ የሆኑ ትእይንቶችን ማየት የተለመደ ሲሆን፤ ለየት ያሉ አልባሳት ከለበሱ ሰዎች አንስቶ በዝግጅቱ ወቅት ክብረ-ወሰን የሰበሩ ሯጮችም አሉ።
በዘንድሮው የለንደን ማራቶን አንድ ሰው ትልቁን ሩጫ ወደ ኋላ በመሮጥ ለማጠናቀቅ መወጠኑ ተነግሯል።
ለማራቶን አዲስ አይደለም የተባለው የ46 ዓመቱ ቶም ሃሪሰን እ.አ.አ.በ2017 እንደ ዝንጀሮ ለብሶ የ26.2 ማይል ውድድሩን ጨርሷል።
ዘንድሮ ደግሞ ለዩክሬን “ስጋትን ማሳየት” አለብኝ በሚል ውድድሩን ወደ ኋላ በመሮጥ አጠናቅቃለሁ ብሏል።
ሀሳቡ ከሩሲያ ጋር እየተደረገ ባለው ጦርነት የተጎዱ ዩክሬናውያንን ለመደገፍ እንደሚረዳ ተስፋ አለኝ ብሏል።
ቶም አብረውት ከሚሮጡት ሯጮች ጋር ላለመጋጨት ሲል በእለቱ ማራቶንን ከኋላ ለመጀመር አቅዷል። ለሀሳቡ መሳካት ልምምድ ሲያደርግ መሰንበቱን ቢቢሲ ዘግቧል።