በሱዳን እየተካሄደ ባለው ጦርነት የውጭ ሀገር ዜጎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸው በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል
በሱዳን፣ በሱዳን ጦር እና በጀነራል ሀምዳን ደጋሎ በሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል የተጀመረው ጦርነት አንድ ሳምንት አልፎታል።
በሱዳን እየተካሄደ ባለው ጦርነት የውጭ ሀገር ዜጎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸው በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።
ጦርነቱ ሰፊ ቦታን በማካለሉ እና የሱዳን ዋና ከተማ የሚገኘው የካርቱም አለምአቀፍ አየርመንገድ የጦር ቀጣና በመሆኑ በሀገሪቱ ያሉ ዲፕሎማቶችን ማስውጣት አስቸጋሪ ነበር።
የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ጫና ቢያደርጉም፣ የተደረሱ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ወደ ተግባር ሳይቀየሩ ቀርተዋል።
ይህን አስቸገሪ ሁኔታ በመቋቋም የተወሰኑ ሀገራት ዜጎቻቸውን ጦርነት እየተካሄደባት ካለችው ሱዱን ማስወጣት ችለዋል።
እስካሁን በተደረገው ጥረት አራት ሀገራት የጦር ቀጣና ከሆነችው ሱዳን ዜጎቻቸውን ማስወጣታቸውን አስታውቀዋል።
እስካሁን ባለው ጥረት አሜሪካ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ኩዌት እና ፈረንሳይ ዜጎቻቸውን እና ዲፕሎማቶቻቸውን ማስወጣት ችለዋል።
ግብጽ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ለወታደራዊ ልምምድ ሱዳን ነበሩ ያለቻቸውን ወታደሮች አብዛኞቹ እንዲወጡ ማድረግ ችላለች።
አሜሪካ ዛሬ ባወጣችው መግለጫ በሱዳን የሚገኙ ሁሉንም ዲፕሎማቶቿን ማስወጣቷን አስታውቃለች።
አሜሪካ በሱዳን የሚገኙ ሁሉንም ዲፕሎማቶች ካስወጣች በኃላ ኢምባሲዋን መዝጋቷን አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን ገልጸዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በካርቱም ኢምባሲ ያለውን ስራ በጊዜያዊነት ማቆማቸውን አስታውቀዋል።
በሱዳን ያሉ የኢምባሲ ሰራተኞችን እንዲያስወጣ ለጦሩ ትዕዛዝ መስጠታቸውን የገለጹት ፕሬዝደንቱ በሂደቱ ተባብረዋል ያሏቸውን ሳኡዲ አረቢያን፣ ኢትዮጵያን እና ጅቡቲን አመስግነዋል።
በትናንትናው እለት ሳኡዲ አረቢያ እና ኩዌት ዜጎቻቸውን ማስወጣታቸውን ገልጸው ነበር።
ሳኡዲ አረቢያ፣ አራት የጦር መርከቦችን በመላክ የራሷን እና የሌሎች ሀገራት ዜጎችን ከፖርት ሱዳን መውሰድ መቻሏን ገልጻለች።
በሱዳን እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንደቀጠለ ነው።
አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ተኩስ እንዲያቆሙ ቢጠይቁም እስካሁን ፍሬ አላፈራም።