የቻድን ድንበር አልፈው የሚገቡ ሱዳናውያን ቁጥር እየጨመረ ነው ተባለ
ባለፈው ሳምንት ብቻ 20 ሺህ የሚጠጉ ሱዳናውያን ቻድ መግባታቸውን የአለም የምግብ ፕሮግራም አስታውቋል
በቻድ ከ400 ሺህ በላይ ሱዳናውያን ጦርነትን ሸሽተው በስደተኛ መጠለያ ካምፖች ይገኛሉ
የአለም ምግብ ፕሮግራም ወደ ቻድ የሚገቡ ሱዳናውያን ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድ ገለጸ።
ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ከ10 ሺህ እስከ 20 ሺህ የሚጠጉ ሱዳናውያን የቻድን ድንበር አልፈው ገብተዋል ብሏል ድርጅቱ።
የጀነራሎቹ ጦርነት ሊበርድ አለመቻሉ የስደተኞቹን ቁጥር ከፍ እንደሚያደርገው ይጠበቃልም ነው ያለው።
በቻድ የአለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተሩ ፔር ሆኖራት፥ “የስደተኞች ማዕበል እንደሚኖር እንጠብቃለን፤ በድንበር ላይ የሚገኙ የቻድ ከተሞችም በሱዳናውያን ይሞላሉ” ሲሉ መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
በሱዳን ከዚህ ቀደም የተነሱ ጦርነቶችን ሽሽት ከ400 ሺህ በላይ ሱዳናውያን የቻድን ድንበር አቋርጠው በ14 የስደተኞች መጠለያዎች ይገኛሉ።
በአሁኑ ወቅት በካርቱምና ሌሎች ከተሞች የቀጠለው ጦርነትም ከ100 ሺህ በላይ ሱዳናውያንን ወደ ቻድ ሊያስድድ እንደሚችል ነው የአለም ምግብ ፕሮግራም የገለጸው።
አሃዙ ከዚህም ከፍ ሊል ስለሚችል ተገቢው ዝግጅት መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።
በጦርነቱ ምክንያት ቤታቸው የተቃጠለባቸውና ሃብት ንብረታቸውን ያጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ህይወታቸውን ለማትረፍ ስደትን መርጠዋል ያሉት የድርጅቱ ዳይሬክተር፥ በርካታ ሴቶችና ህጻናትም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል።
ሱዳናውያኑ በቻድ የተጠለሉባቸው አካባቢዎችም በርሃማ ስለሆኑ በፍጥነት የመጠጥ ውሃ እና ምግብ አቅርቦት ለማድረስ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ነው ያነሱት።
ከሱዳን ጋር ከ 1 ሺህ 400 ኪሎሜትር በላይ ድንበር የምትጋራው ቻድ ጦርነቱ እንደተጀመረ የድንበር መተላለፊያዎቼን ዘግቻለሁ ብትልም በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ድንበር አቋርጠው እየገቡ ነው ተብሏል።