ብቸኝነት ያማረራቸው ስፔናዊ እስር ቤት ለመግባት እየተማጸኑ ነው
የ60 አመቱ ጁስቶ ማርኪዩዝ ከድብርት ለመውጣት ያለኝ ብቸና አማራጭ እስር ቤት መግባት ነው ብለዋል
ወንጀል መፈጸም አልፈልግም ያሉት አዛውንት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ ለቀናት እስር ቤት በር ላይ ናቸው
በስፔን ብቸኝነት እና ህመም እያንገላታኝ ነው ያሉ አዛውንት እስር ቤት ለመግባት ተማጽኖ ማቅረባቸው ተሰምቷል።
ትውልና እድገታቸው በግራናዳ የሆነው የ60 አመቱ አዛውንት ጁስቶ ማርኪዩዝ በማላጋ በሚገኝ እስር ቤት ለመግባት በር ላይ የተማጽኖ ጽሁፍ ይዘው ቆመዋል ነው የተባለው።
ማርኪዩዝ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት “ወንጀል መፈጸም አልፈልግም፤ በፈቃዴ እስር ቤት መግባት እፈልጋለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።
አዛውንቱን ማረሚያ ቤት መግባት ያስመኛቸው ብቸኝነት እና ድብርት መሆኑንም ይገልጻሉ።
ካንሰር፣ የልብ ህመም፣ ድብርት እና ፍርሃት የተደራረበባቸው አዛውንት “24 ስአት ሙሉ ብቸኛ መሆን ሰልችቶኛል” ብለዋል።
“ምንም የሚረዳኝ ሰው አለገኘሁም፤ አሁን ያለኝ ብቸኛ አማራጭ ማረሚያ ቤት ውስጥ መግባት ነው” የሚሉት ማርኪዩዝ፥ ካለባቸው ድብርትና ህመም ጋር በተያያዘ ወንጀል ውስጥ እንዳይገቡ እስር ቤት መግባቱን መምረጣቸውን ያነሳሉ።
የአምስት ልጆች አባት የሆኑት እኝህ አዛውንት ለወራት ከሰዎች ጋር ሲነጋገሩ አልታየም የሚለው የስፔኑ የዜና ወኪል ኢኤፍኢ፥ በአደንዛዥ እጽ ዝውውር ለሁለት አመት ገደማ ታስረው እንደነበር ያስታውሳል።
ማርኪዩዝ ላለፉት ሶስት አስርት አመታት ከዚህ ወንጀል መራቃቸውን በመጥቀስ የማላጋ በሚገኘው እስር ቤት አመራሮች ጥያቄያቸውን እንዲቀበሏቸው እየወተወቱ ነው ተብሏል።
እስር ቤት መግባት ካልተፈቀደልኝ ከግቢ ውጭ ተቃውሞዬን አሰማለሁ ሲሉም ዝተዋል።
በርካቶች በተለያየ ምክንያት እስር ቤት መግባት ይፈልጋሉ የሚለው የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ፥ ጁስቶ ማርኪዩዝ ግን ወንጀል ሰርተው መግባትን ያለመፈለጋቸውና ብቸኝነትን መርሻ መንገድ ማድረጋቸው የተለየ እንደሚያደርገው አብራርቷል።