የሎስ አንጀለሱ ሰደድ እሳት አደጋ ምን ላይ ይገኛል፤ ምን አዳዲስ ክስተቶችስ አሉ?
የኢቶንና ፓላሲደስ ጨምሮ በአራት ስፍራዎች ያሉ የሰደድ እሳቶች አሁንም እየነደዱ ነው
በእሳት የተቃጠሉ ቦታዎች ዝናብ እንደሚያገኙ መተንበዩን ተከትሎ የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋ ስጋት ተደቅኗል
በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛት በምትገኘው ሎስ አንጀለስ ከተማ እና አካባቢው ከ19 ቀናት በፊት ከተቀሰቀሰው እሳት አሁንም እንደቀጠለ ነው።
የእሳት አደጋው በአብዛኛው ስፍራ በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚደረገው ጥረት አሁንም እንደቀጠለ ነው የአካባው ባለስልጣናት ያስታወቁት።
ሎስ አንጀለስ ከተማ እና አካባቢው ከ19 ቀናት በፊት ከተቀሰቀሰው እሳት ውስጥ ከባድ የተባሉት የኢቶንና ፓላሲደስ እሳቶችን ጨምሮ አራ ት የሰደድ እሳቶች አሁንም እየነደዱ መሆኑም ተነግሯል።
የሰደድ እሳቶቹ ምን ላይ ይገኛሉ?
ላጉና እሳት
ላጉና እሳት 33.58 ሄክታር መሬት ያቃጠለ ሲሆን፤ እስከ ትናንት ቅዳሜ ምሽት ድረስ 98 በመቶውን መቆጣጠረ መቻሉ ተነግሯል።
በላጉና እሳት በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም የተባለ ሲሆን፤ የተቃጠሉ ህንጻዎችና መኖሪያ ቤቶች የሉም ተብሏል።
ፓሊሳደስ እሳት
በሎሳንጀለስ ከተቀሰቀሱ የሰደድ እሳቶች ውስጥ ግዙፉ የተባለው የፓሊሳደስ እሳት እስካሁን ከ9 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት አካሏል።
የሰደድ እሳቶቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚደረገው ጥረት አሁን መቀጠሉን እና እስከ ትናንት ቅዳሜ ምሽት ድረስ 84 በመቶውን መቆጣጠረ መቻሉ ተነግሯል።
በፓላሲደስ እሳት እስካሁን የ11 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፤ ከ6 ሺህ 800 በላይ ህንጻዎችና መኖሪያ ቤቶች በእሳት ተበልተዋል።
ኢቶን እሳት
በሎሳንጀለስ ከተቀሰቀሱ የሰደድ እሳቶች ውስጥ ግዙፉየኢቶን እሳት እስካሁን 5 ሺህ 600 ሄክር መሬት አካሏል።
የሰደድ እሳቶቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚደረገው ጥረት አሁን መቀጠሉን ነው የካፎርኒያ ግዛት የመንግስት ኃላፊዎች ያሳወቁ ሲሆን፤ እስከ ትናንት ድረስም 95 በመቶውን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል።
በኢቶን እሳት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 17 የደረሰ ሲሆን፤ ከ9 ሺህ 400 በላይ መኖሪያ ቤቶች እና ህንጻዎች በእሳቱ ተበልተዋል።
ሂዩስ እሳት
ባሳለፍነው ረቡዕ ምሽት እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው ሂዩስ እሳት ከ4 ሺህ 200 ሄክታር በላይ ሲያቃጥል እስካሁን 90 በመቶውን መቆጣጠር ተችሏል።
የጎርፍና የመሬት መንሸራተት ስጋት
በካፎርኒያ ግዛት የምትገኘው ሎስ አንጀለስ ከተማ እና አካባቢውከረጅም ጊዝ በኋላ ከሰሞኑ ዝናብ እንደሚያገኙ ትንብያዎች አመላክተዋል።
ሆኖም ግን ዝናቡ ከመልካም ዜና በተጨማሪ ሌላ ስጋትን ደቅነኗል የተባለ ሲሆን፤ በተለይም የእሳት አደጋ የተከሰተባቸው አካባቢዎች የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋ ስጋት ተደቅኖባቸዋል ነው የተባለው።