የሎስ አንጀለስ ባለሀብቶች ቅንጡ ቤታቸውን ከእሳት ለመጠበቅ በሰዓት 2 ሺህ ዶላር እየከፈሉ ነው
ባለሀብቶቹ የሚሊየን ዶላር ቅንጡ ቤቶቻውን ለመጠበቅ የግል የእሳት አደጋ ተቆጣጣሪ ቀጥረዋል
ሎስ አንጀለስን እያደደ ያለው እሳት አሁንም የቀጠለ ሲሆን እሳቱን ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት ቀጥሏል
በአሜሪካዋ ሎስ አንጀለስ ከተማ የሚኖሩ ባለሀብቶችና ታዋቂ ሰዎች ቅንጡ መኖሪያ ቤታቸውን ከእሳት ለመታደግ በሰዓት 2 ሺህ ዶላር እየከፈሉ ነው ተብሏል።
የሎስ አንጀለስ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ባለሀብቶች እና ታዋቂ ሰዎች የሚሊየን ዶላር ቅንጡ ቤታቸውን ከእሳት ለመታግ የግል የእሳት አደጋ ተቆጣጣሪ ድርጅቶችን በውድ ዋጋ ቀጥረዋል ነው የተባለው።
በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛት የተቀሰቀሰው ሰደድ እሳት 11ኛ ቀኑን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንረታው አፈናቅሏል።
በሎስ አንጀለስ ከሳምንት በፊት በተቀሰቀሰው እሳት ከ12 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች እና ህንጻዎች በእሳት እንደተበሉ ተነግሯል።
በእሳት ከተበሉ መኖሪያ ቤቶች መካከል የተቃዋቂ የሆሊውድ ተዋናዮች ቅንጡ እና ውድ መኖሪያ ቤቶች እንደሚገኙበትም ይታወቃል።
እስካሁን መኖሪያ ቤታቸው ጋር እሳት ያለደረሰባቸው በከተማዋ ውስጥ የሚሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸው ቅንጡ መኖሪያ ቤት ባለቤት የሆኑ ባለሃብቶች እና ታዋቂ ሰዎች በውድ ዋጋ የግል የእሳት አደጋ መከላከል ባለሙያዎች ቀጥረዋል።
ባለሀብቶቹ የግል የእሳት አደጋ ተከላካይ ድርጅቶችን በሰዓት 2 ሺህ ዶላር በመክፈል ንረታቸውን እያስጠበቁ መሆኑን ተከትሎም ትችቶችን እያስተናዱ ነው።
ሁሉም የእሳት አደጋ ተከላካይ ሰራተኞች እሳቱን ለማጥፋት ዋጋ እየከፈሉ ባለበት ወቅት ባለሀብቶቹ እንዲህ ማድረጋቸው ተገቢነት የለውም በሚል በበርካቶች ተተችቷል።
ባለሀብቶቹ የግል የእሳት አደጋ ተከላካዮችን በውድ ዋጋ መቅጠራቸው የከተማ አስተዳሩ ይጠብቃል የሚል እምት ስለሌላውም ነውም ተብሏል።
በአሁኑ ወቅት እሳቱ ምን ላይ ይገኛል?
በአሁኑ ወቅት በ6 ቦታዎች እየነደደ ያለውን እሳት ለማጥትፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተነግሯል። እሳቶቹ የሚገኘበት ስፍራም፤
የፓሊሳድስ እሳት፤ ከሶስት ዋና ዋና የሰደድ እሳቶች ትልቁ ሲሆን፤ 9 ሺህ 596 ሄክታር አቃጥሏል፤ አሁን ላይ 21 በመቶውን መቆጣጠርም ተችሏል። የእሳት አደጋ ሰራተኞች እሳቱ የጌቲ ሴንተር ሙዚየም መኖሪያ ወደሆነው ወደ ብሬንትዉድ እንዳይዛመት የመከላከል ስራ እየሰሩ ነው።
ኢቶን እሳት፡ ከሎስ አንጀለስ በሰተምስራቅ የሚገኝ፤ ይህ ሰደድ እሳት ከሞት አንፃር እጅግ አጥፊው ሲሆን፤ በኢቶን እሳት 16 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። እሳቱ 5 ሺህ 712 ሄክታር መሬት አቃጥሏል፤ አሁን ላይ 45 በመቶውን መቆጣጠርም ተችሏል።
ሀረስት እሳት፤ በሰሜን ሳን ፈርናንዶ አቅራቢያ የተቀሰቀሰው ይህ እሳት 323 ሄክታር መሬት አቃጥሏል። የእሳት አደጋ ተከላካይ ሰራተኞች አሁን ላይ 98 በመቶውን ተቆጣጥረዋል፤ ሙሉ ለሙሉ በቅጥጥር ስር ለማድረግ ተቃርበዋል.
አውቶ እሳት፤ በቬንቱራ ካውንቲ ውስጥ የተቀሰቀሰው እሳት በፍጥነት 24 ሄክታርመሬት አካሏል። የእሳት አደጋ ተከላካዮች የእሳቱን መዛመት አቁመው ነበር፣ እስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ የእሳቱን 85 በመቶው በቁጥጥር ስር አውለዋል።
ሊትል ማውንቴን እሳት፤ በሎስ አንጀለስ ምስራቃዊ ክፍል የሚገኘው እሳቱ አዲስ የተቀሰቀሰ ሲሆን በፍጥነት 12 ሄክታር መሬት አቃጥሏል። በበርካታ ህንጻዎች እና መኖሪያ ቤቶች ላይ ስጋት የደቀነው እሳቱ አሁንም በቁጥጥር ስር አልዋለም።