በሎስ አንጀለስ ከሁለት ሳምት በፊት የተቀሰቀሱት የኢቶንና ፓላሲደስ እሳቶች አሁንም እየነደዱ ነው።
በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛት በምትገኘው ሎስ አንጀለስ ከተማ ሰሜናዊ ክፍል ላይ ባሳለፍነው ረቡዕ አዲስ እና ግዙፍ የሆነ የሰደድ እሳት መቀስቀሱ ተነግሯል።
በከባድ ፍጥነት በሚጓጓዝ ነፋስ እየተፋመ ያለው አዲሱ ሰደድ እሳት ሌሊት ላይ የተቀሰቀሰ ሲሆን፤ እስካሁን ከ4 ሺህ 118 ሄክታር በላይ መሬት ማካለሉ ተነግሯል።
አዲስ የተቀሰቀሰውን የሰደድ እሳት ተከትሎ 31 ሺህ ሰዎች አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ ከመኖሪያቸው እንዲለቁ የታዘዙ ሲሆን፤ 16 ሺህ ሰዎች ደግሞ በተጠንቀቅ ላይ እንዲሆኑ ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል።
በርካታ የእሳት አደጋ መከላከያ አውሮፕላኖች እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ የእሳት አደጋ ሰራተኞች ከሎስ አንጀለስ በስተሰሜን በሚገኘው ካስታይክ ሀይቅ አካባቢ በፍጥነት እየነደደ ያለውን እሳት ለመቆጣጠር እየጣሩ መሆኑም ተገልጿል።
ከ4 ሺህ በላይ የእሳት አደጋ ሰራኞች እሳቱን የመከላከል ስራ ላይ ተሰማርተዋል የተባለ ሲሆን፤ እስካሁን በተደረገው ብርቱ ጥረተም እሳቱ እዳይዛመት ማቆም ተችሏል።
በተጨማሪም ሎስ አንጀለስ ከተማ ሰሜናዊ ክፍል ላይ አዲስ ከተቀሰቀሰው ሰደድ እሳት ውስጥ 24 በመቶውን መቆጣጠር አንድተቻለም ነው የከተማዋ የእሳት አደጋ መከላከል ባለስልጣናት ያስወቁት።
በተያያዘ በሎስ አንጀለስ ከተማ እና አካባቢው ከ16 ቀናት በፊት ከተቀሰቀሰው እሳት ውስጥ ከባድ የተባሉት የኢቶንና ፓላሲደስ እሳቶች አሁን እየነደዱ መሆኑም ተነግሯል።
የኢቶን እሳት እስካሁን 5 ሺህ 600 ሄክር መሬት ሲያካልል፤ ፓላሲደስ እሳት ደግሞ ከ9 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት አካሏል።
የሰደድ እሳቶቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚደረገው ጥረት አሁን መቀጠሉን ነው የካፎርኒያ ግዛት የመንግስት ኃላፊዎች የተናገሩት።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰደድ እሳቱ ያስከተለውን ጉዳት ለመመልከት በነገው እለት አርብ ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑ ታውቋል።
እሳት አደጋው ያስከተለው ጉዳት ምን ይመስላል?
በአሜሪካዋ ሎስ አንጀለስ ከተማ የተቀሰቀሰው የሰደድ እሳት በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን እንደቀጠለ ነው።
በዚህም መሰረት የእሳት አደጋው ከተቀሰቀሰበት እለት አንስቶ እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 28 መድረሱ ተነግሯል።
በተጨማሪም ከ16 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ያካለለው የእሳት አደጋው እስካሁን ከ16 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶችን እና ህንጻችንም በልቷል።
በዚህ መሰረት በኢቶን እሳት 10 ሺህ መኖሪያ ቤቶች እና ህንጻዎች፣ በፓሊሳደስ እሳት 6 ሺህ 51 ቤቶች ህንጻዎች እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ባሉ የእሳት አደጋዎች 788 ቤቶችና ህንጻዎች በእሳት መበላታቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ትናት ጠዋት ባወጡት ሪፖርት አመላክተዋል።
የፓሊሳድስ እና ኢቶን ሰደድ እሳት ዛሬም መንደዱን የቀጠለ ሲሆን፤ የፓሊሳድስ እሳትን 72 በመቶ እንዲሁም የኢቶን እሳትን ደግሞ 95 በመቶ መቆጣጠር መቻሉም ተነግሯል።
በአደጋው የደረሰው ጠቅላላ ውድመት እና የኢኮኖሚ ኪሳራ 250 ቢሊዮን ዶላር ገደማ መሆኑን አኩ ዌዘር ገምቷል።
የሎስ አንጀለስ ሰደድ እሳት ሁሪካን ካትሪና ካደረሰው አደጋ በመብለጥ በአሜሪካ ታሪክ እጅግ ከባድ የተፈጥሮ አደጋ ሆኖ ተመዝግቧል።