ከዚህ በፊት የሰው ልጅ ከ3 ሺህ 500 ዓመት ጀምሮ መሳሳም የፍቅር መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል ተብሎ ይታመን ነበር
መሳሳም የፍቅር መግለጫ ሆኖ የጀመረው የት ይሆን?
መሳሳም ከፍቅር መገለጫዎች መካከል አንዱ ሆኖ ይገለጻል። ይሁንና መሳሳም የተጀመረው የት እና መቼ ነው የሚለው ጉዳይ ተመራማሪዎችን ሲያጨቃጭቅ ቆይቷል።
እስከዛሬ በነበረው መረጃ መሰረት የሰው ልጅ ከ3 ሺህ 500 ዓመት በፊት ጀምሮ መሳሳምን እንደፍቅር መገለጫ አድርጎ ይወስድ እንደነበር ብዙሀኑን የማህበረሰብ ሳይንስ ተመራማሪዎችን ያስማማ ነበር።
አሁን ደግሞ ከዚህ በፊት መሳሳም ተጀምሯል ተብሎ ከሚያመንበት አንድ ሺህ ዓመት ቀድሞ መጀመሩን የሚያሳይ ማስረጃ መገኘቱ ተገልጿል።
በዚህ መረጃ መሰረት በቀድሞ ስሙ ሜሶፖታሚያ በአሁኑ ደግሞ ኢራቅ እና ሶሪያ አካባቢዎች በተገኘ ጥናት መሳሳም እንደ አንድ የፍቅር መገለጫ ተደርጎ ይቆጠር ነበር።
ከዚህ በፊት በተደረገው ጥናት መሳሳም እንደፍቅር መገለጫ ሆኖ የተጀመረው በደቡባዊ እስያ እንደሆነ ይገመት እንደነበር ተገልጿል።
የኮፐንሀገን ማህበረሰብ ሳይንስ ተመራማሪው ዶክተር ትሮልስ ፓንክ አርቦል እንዳሉት መሳሳም በተወሰኑ ቦታዎች ብቻ የተጀመረ እና ቀስ በቀስ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የተስፋፋ እንዳልሆነ ተናግረዋል ሲል ስካይ ኒውስ ዘግቧል።
አሁን በኢፍራተስ እና ጢግሮስ ወንዝ ዳር ባሉ ቦታዎች ጥንዶች መሆናቸውን የሚያሳዩ የሸክላ ላይ ማስረጃዎች ከዚህ በፊት መሳሳም ተጀምሮበታል የተባለውን ጊዜ እና ቦታ ትክክል አለመሆኑን ማሳየቱ ተገልጿል።
በዚህ ማስረጃ መሰረትም መሳሳም እንደ ፍቅር መገለጫ ተደርጎ የተቆጠረበት ጊዜ ቢታወቅም እዚህ ቦታ እና በሆነ ማህበረሰብ አማካኝነት ተጀመረ ማለት እንደማይቻል ተመራማሪው ተናግረዋል ።