በወር 500 ዩሮ እና በላይ ደመወዝ ይጨመርልን ያሉ የሉፍታንዛ አየር መንገድ ሰራተኞች ስራ አቆሙ
አየር መንገዱ በሰራተኞች ስራ ማቆም ምክንያት 200 ሺህ መንገደኞች በረራቸው ተስተጓጉሏል
የሉፍታንዛ አየር መንገድ እስከ 90 በመቶ የዕለታዊ በረራ ተሰርዟል ተብሏል
በወር 500 ዩሮ እና በላይ ደመወዝ ይጨመርልን ያሉ የሉፍታንዛ አየር መንገድ ሰራተኞች ስራ አቆሙ፡፡
የዓለማችን ግዙፍ አየር መንገድ የሆነው የጀርመኑ ሉፍታንዛ በተደጋጋሚ በሚደረጉ የሰራተኞች ስራ ማቆም አድማ ምክንያት በረራዎችን ለመሰረዝ ተገዷል፡፡
በዛሬው ዕለትም ሰራተኞች ባደረጉት ተመሳሳይ የስራ ማቆም አድማ ምክንያት እስከ 90 በመቶ የሚደርሱ ዕለታዊ በረራዎቹን እንደሰረዘ አስታውቋል፡፡
በበረራዎቹ መሰረዝ ምክንያትም 200 ሺህ መንገደኞች በረራቸው እንደተስተጓጎለባቸው የተገለጸ ሲሆን አየር መንገዱ ለተፈጠረው ችግር ካሳ እንደሚሰጥ ገልጿል፡፡
ፍራንክፈርት፣ ሙኒክ፣ ኮሎኝ-ቦን፣ ሀምቡርግ፣ ዱስልድሮፍ እና ስቱትጋርት ኤርፖርቶች በረራቸው በተሰረዘባቸው መንገደኞች ተጨናንቋል፡፡
የጀርመኑ ሉፍታንዛ አየር መንገድ 800 በሪራዎችን ሰረዘ
በሰራተኞች ስራ ማቆም አድማ ምክንያት በረራ ሲቋረጥ በአንድ ወር ውስጥ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሆነ ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ የሉፍታንዛ አየር መንገድ የስራ ማቆም አድማውን ያካሄዱት የ12 በመቶ ወይም በትንሹ የ500 ዩሮ ወርሃዊ ደመወዝ እንዲጨመርላቸው በሚል ነው፡፡
የጉዞ ቲኬት ገዝተው የነበሩ እና በስራ ማቆም አድማው ምክንያት በረራቸው የተስተጓጎለባቸው መንገደኞች ገንዘባቸው እንደሚመለስላቸው አልያም ሌላ በረራ ቲኬት መግዛት እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡
25 ሺህ ሰራተኞች ያሉት ሉፍታንዛ የበረራ አስተናጋጆች፣ የጥገና ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለሙያዎቹ የስራ ማቆም አድማ በማድረግ ላይ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡