አየር መንገዱ ከአንድ ወር በፊት በገጠመው የሰራተኞች አድማ ከአንድ ሺህ በላይ በረራዎችን መሰረዙ ይታወሳል
የጀርመኑ ሉፍታንዛ አየር መንገድ ፓይለቶች ሰራ ማቆም አድማ እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን ተከትሎ 800 በረራዎችን መሰረዙን አስታውቋል።
ከአምስት ሺህ በላይ የሉፍታንዛ አየር መንገድ ፓይለቶች የስራማቆም አድማ እንደሚያደርጉ ገለጹ።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ የዓለም ምግብና ነዳጅ ዋጋ በማሻቀብ ላይ ይገኛል።
የዋጋ ግሽበትን ተከትሎም በርካታ ሀገራት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ናቸው።
ሩሲያ 40 በመቶ የአውሮፓ ሀገራትን ነዳጅ ፍላጎት የምትሸፍን ቢሆንም ምዕራባውያን ሀገራት በሩሲያ ላይ ማዕቀቦችን በመጣል ላይ ናቸው።
በዚህና ሌሎች ምክንያቶች በአውሮፓ የምርቶች ዋጋ እና አቅርቦት በመጨመሩ ዜጎች መንግስቶቻቸው የተለያዩ የኢኮኖሚ ማረጋጊያ እርምጃዎች እንዲወስዱላቸው እየጠየቁ ይገኛሉ።
የአየር መንገዱ ሰራተኞች የሆኑ ከአምስት ሺህ በላይ አውሮፕላን አብራሪዎች ወይም ፓይለቶች ከነገ ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ እንደሚያደርጉ ሮይተርስ ዘግቧል።
የአየር መንገዱ ፓይለቶች የስራ ማቆም አድማ የሚያደርጉት በነዳጅ ዋጋ መናር ምክንያት ኑሮ ስለተወደደ ደመወዝ ይጨመርልን በሚል ነው።
ይህን የታቀደውን የፓይለቶች አድማ ተከትሎም የሉፍታንዛ አየር መንገድ ከወዲሁ በረራዎች እንዳይሰረዙ ከሰራተኛ ማህበራት ጋር ድርድር በማድረግ ላይ መሆኑ ተገልጿል።
የአየር መንገዱ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል የሆኑት ሚካኤል ኒጌማን ኩባንያው ለሰራተኞቹ ከወርሀዊ ደመወዛቸው ውጪ ለመሰረታዊ ፍላጎቶች በሚል በወር 900 ዩሮ በመክፈል ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ከአንድ ወር በፊት በተለያዩ የጀርመን ግዛቶች ባሉ አውሮፕላን ጣቢያዎች ያሉ ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ባደረጉት የስራ ማቆም አድማ ከአንድ ሺህ በላይ በረራዎቹን መሰረዙ ይታወሳል።
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የዋጋ ግሽበት ያጋጠመ ሲሆን በቤልጂየም፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ስፔን እና ጣልያን በአንጻራዊነት ከፍተኛ የኑሮ ውድነቱን ተከትሎ ዜጎች ማሻሻያ እንዲደረግ በመንግስታቸው ላይ ተጽዕኖ በማድረስ ላይ ናቸው ተብሏል።