የሉፍታንዛ አየር መንገድ ሰራተኞች ደመወዝ ይጨመርልን በሚል የአንድ ቀን አድማ ላይ ናቸው
የጀርመኑ ሉፍታንዛ አየር መንገድ ከ100 በላይ በረራዎችን መሰረዙ ተገልጿል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ የዓለም ምግብና ነዳጅ ዋጋ በማሻቀብ ላይ ይገኛል።
የዋጋ ግሽበትን ተከትሎም በርካታ ሀገራት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ናቸው።
ሩሲያ 40 በመቶ የአውሮፓ ሀገራትን ነዳጅ ፍላጎት የምትሸፍን ቢሆንም ምዕራባውያን ሀገራት በሩሲያ ላይ ማዕቀቦችን በመጣል ላይ ናቸው።
በዚህና ሌሎች ምክንያቶች በአውሮፓ የምርቶች ዋጋ እና አቅርቦት በመጨመሩ ዜጎች መንግስቶቻቸው የተለያዩ የኢኮኖሚ ማረጋጊያ እርምጃዎች እንዲወስዱላቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው።
የዓለማችን ግዙፍ የአቪዬሽን ተቋም የሆነው የጀርመኑ ሉፍታንዛ አየር መንገድ ሰራተኞች የአንድ ቀን የስራ ማቆም አድማ መምታታቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል።
ሰራተኞቹ ድንገቴ ሳይሆን የታቀደ አድማ የመቱት ኩባንያው የተጠየቀውን የደመወዝ ማስተካከያ እንዲያደርግ በማሰብ ነው ተብሏል።
አድማውን ተከትሎም የሉፍታንዛ አየር መንገድ በመቶዎች የሚቆጠሩ በረራዎቹን ለመሰረዝ ተገዷል ተብሏል።
በተለያዩ የጀርመን ግዛቶች ባሉ አውሮፕላን ጣቢያዎች ያሉ ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአየር መንገዱ ሰራተኞች አስቀድመው አድማ እንደሚመቱ አስጠንቅቀው ነበርም ተብሏል።
ሰራተኞቹ አየር መንገዱ የ9 ነጥብ 5 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ እንዲያደርግላቸው የጠየቁ ሲሆን ጥያቄያቸው ካልተመለሰ ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ ዘገባው አክሏል።
አሁን እየተመዘገበ ያለው የዋጋ ግሽበቱ በአውሮፓ ታሪክ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ላይ እንዳለ የተገለጸ ሲሆን በቤልጂየም፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ስፔን እና ጣልያን በአንጻራዊነት ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት መታየቱን ተከትሎ ዜጎች ማሻሻያ እንዲደረግ በመንግስታቸው ላይ ተጽዕኖ በማድረስ ላይ ናቸው ተብሏል።