ኢማኑኤል ማክሮን፤ ፊንላንድ እና ስዊድን ኔቶን ለመቀላቀል ያቀረቡትን ጥያቄ በፊርማቸው አጸደቁ
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደንም ሀገራቱ የኔቶ አባል እንዲሆኑ ፈርመዋል
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት የሀገራቱ ኔቶን መቀላቀል ለአውሮፓ ጸጥታ መጠናከር ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ኔቶን ለመቀላቀል ያቀረቡትን ጥያቄ መቀበላቸውን በፊርማቸው አረጋገጡ፡፡
ኢማኑኤል ማክሮን ሁለቱ ሀገራት የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ዳን ድርጅትን (ኔቶ) ለመቀላቀል ያቀረቡትን ጥያቄ በይፋ ተቀብለዋል፡፡ ቀደም ሲል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፊንላንድ እና ስዊድን ኔቶን ለመቀላቀል ያቀረቡትን ጥያቄ በፊርማቸው ማጽደቃቸው ይታወሳል፡፡
ኢማኑኤል ማክሮን የሁለቱ ሀገራት ኔቶን ለመቀላቀል መፈለግ ተቋሙን እንደሚያጠናክር ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡ ሀገራቱ ይህንን ጸጥታ ተቋም መቀላቀላቸው ደህንነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚያግዛቸውም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
የአውሮፓን ጸጥታ የበለጠ ጠንካራ ለማድረግ የሁለቱ ሀገራት መምጣት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ሲል የኤሊዜ ቤተ መንግስት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ የፈረንሳይ ታችኛው ምክር ቤት ነሐሴ ሶስት ቀን ፊንላንድ እና ስዊድን ኔቶን እንዲቀላቀሉ ቀረበውን ሃሳብ ማጽደቃቸው ይታወሳል፡፡
ሁለቱ ሀገራት የኔቶ አባላት ለመሆን ሁሉም አባል ሀገራት በየሀገራቸው ማጽደቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን ላይ ከ 30 የኔቶ አባል ሀገራት መካከል 20 የሚሆኑት ሁለቱም ሀገራት የኔቶ አባል እንዲሆኑ ፈቅደዋል፡፡ ፊንላንድ እና ስዊድን የኔቶ አባል ሀገራት ለመሆን ጥያቄ ያቀረቡት በፈረንጆቹ ግንቦት 18 ቀን 2022 ነበር፡፡
እስካሁን የሀገራቱን የኔቶ አባል መሆን ተቃውማ የነበረችው ቱርክ የነበረች ቢሆንም አሁን ግን ተቃውሞዋን እንደተወች እየተገለጸ ነው፡፡
ሩሲያ፤ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ወደ ምስራቅ አውሮፓ የሚያደርገውን መስፋፋት እንደምትቃወም ቀደም ብላ መግለጿ ይታወሳል፡፡ ለአብነትም ዩክሬን ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ አስገብቷታል፡፡