ሩሲያ፤ ፊንላንድና ስዊድን ኔቶን ለመቀላቀል መወሰናቸውን ተከትሎ የአፀፋ እርምጃ መውሰድ ጀመረች
ፊንላንድና ስዊድን በያዝነው ሳምንት ኔቶን ለመቀላቀል በይፋ አመልክተዋል
ሩሲያ በምእራብ ወታደራዊ ቀጠና ውስጥ 12 አዳዲስ እዞችን እንደምታቋቁም አስታውቃለች
ሩሲያ፤ ፊንላንድ እና ስዊድን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) ለመቀላቀል መወሰናቸውን ተከትሎ የአፀፋ እርምጃ መውሰድ መጀመሯን አስታወቀች።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጊ ሾይጉ በሰጡት አስተያየት፤ ፊንላንድ እና ስዊድን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) ለመቀላቀል መወሰናቸው በሩሲያ ድንበር አካባቢ ወታደራዊ ስጋቶች እንዲጨምሩ ያደርጋል ብለዋል።
ይህንን ተከትሎም ሩሲያ አስፈላጊ የሆኑ የአፀፋ እርምጃዎችን መውሰድ እንደጀመረች መግለጻቸውን ኢንትራፋክስ የዜና ኤጀንሲ ዘግቧል።
በዚህም ሩሲያ በምእራብ ወታደራዊ ቀጠኛ ላይ ተጨማሪ 12 የጦር እዞችን በማቋቋም ምለሽ እንደምትስጥም ነው የመከላከያ ሚኒስትሩ ያስታወቁት።
ፊንላንድ እና ሰዊድን ባለፍነው ረቡዕ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) ለመቀላቀል በይፋ ማመልከታቸው ይታወሳል።
ፊንላንድ እና ስዊድን ውሳኔ ተከትሎ በኋላም የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፒቲን በሰጡት አስታያት ሀገራቱ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን ቢቀላቀሉም ለሀገራቸው ስጋት እንደማይሆን ገልጸዋል።
ቭላድሚር ፑቲን ሁለቱ ሀገራት ድርጅቱን መቀላቀላቸው ለሩሲያ ስጋት ባይሆንም ምላሽ ሊያሰጥ እንደሚችል መናገራቸውም ይታወሳል።
የፖለቲካ ሰዎች የስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን መቀላቀል አሁን በዩክሬን ያለውን ጦርነት ወደ ሌሎች ሀገራት ሊያዛምተው እንደሚችል እየተነበዩ ነው።
በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት መነሻ የዩክሬን ኔቶን ለመቀላቀል መወሰኗ መሆኑ ይታወሳል። ይህ ደግሞ አሁን ኔቶን መቀላቀል የፈለጉትን ስዊድን እና ፊንላንድን ከሩሲያ ጋር ጦር እንዳያማዝዛቸው ተፈርቷል።
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)አሜሪካ እና ካናዳን ጨምሮ በድምሩ 30 አባል ሀገራት አሉት። ከዚህ ውስጥ 28ቱ የአውሮፓ ሀገራት ናቸው።
መቀመጫውን ቤልጄም ብራሰልስ ያደረገው ኔቶ አሁን ላይ 34ኛ የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት ጀንስ ስቶልተንበርግ እየተመራ ይገኛል።