የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ቴል አቪቭ ገቡ
ፕሬዝዳንቱ በእስራኤልና ፍልስጤም መካከል “ትክክለኛ የሰላም ንግግር” እንዲጀመር ጥሪ ያቀርባሉ ተብሏል
ማክሮን በራማላህ ከፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ሙሀሙድ አባስ ጋር ይወያያሉ
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሀገራቸው ለእስራኤል ያላትን አጋርነት ለማሳየት ዛሬ ቴል አቪቭ ገብተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ቴል አቪቭ እንደገቡ በሃማስ ጥቃት ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ትውልደ እስራኤላውያን የፈረንሳይ ዜጎችን አነጋግረዋል።
ማክሮን በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ “የእስራኤልን ሀዘን እንጋራለን” የሚል ጽሁፍ አስፍረዋል።
ፕሬዝዳንቱ በእስራኤል ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ሊሎች የሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሏል።
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው ማክሮን ወደ ራማላህ በማቅናትም ከፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ሙሀመድ አባስ ጋር ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሃማስ ከ18 ቀናት በፊት በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ፈጽሞ ከ220 በላይ ሰዎችን ማገቱ ከተገለጸ ወዲህ ሰባት ፈረንሳውያን የገቡበት አልታወቀም።
በሃማስ ከታገቱት ውስጥ አንዷ ፈረንሳዊ መሆኗ የተረጋገጠ ሲሆን ቀሪዎቹም በቡድኑ ተይዘዋል የሚል እምነት አለ።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከእስራኤልና ፍልስጤም መሪዎች ጋር በሚያደርጉት ውይይትም በሃማስ የታገቱ ሰዎች ስለሚለቀቁበት ሁኔታ ይመክራሉ ብሏል ፍራንስ 24 በዘገባው።
እስራኤል በጋዛ በንጹሃን ላይ የምትፈጽመውን የአየር ድብደባ እንድታቆም ጥሪ ያቀርባሉ ተብሎም ይጠበቃል።
በኢራን የሚደገፉት የሄዝቦላህ ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር የጀመሩት ውጊያ ቀጠናዊ ውጥረቱን እንደሚያባብሰው የገለጸው የፕሬዝዳንት ማክሮን ጽህፈት ቤት፥ ማክሮን በእስራኤልና ፍልስጤም መካከል “ትክክለኛ የሰላም ንግግር” እንዲጀመር ሃሳብ ያቀርባሉ ብሏል።
የሰላም ሃሳቡ ፍልስጤም ነጻ ሀገር እንድትሆንና የቀጠናው ሀገራትም ለእስራኤል ደህንነት ዋስትና እንዲሰጡ የሚጠይቅ ነው ተብሏል።
ማክሮን ከዮርዳኖስ ንጉስ አብዱላህ ሁለተኛ እና ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋርም የመካከለኛው ምስራቅ ውጥረትን ለማርገብ የሚያስችል ውይይት እንደሚያደርጉ የኤሊዜ ቤተመንግስት ገልጿል።