የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት እና የሀገራት የሀይል አሰላለፍ ምን ይመስላል?
ጀርመንና ፈረንሳይን ጨምሮ ስድስት ሀገራት ከእስራኤል ጎን እንደሚቆሙ አሳውቀዋል
ኢራን፣ ኳታር፣ ቱርክ እና ሌሎችም ሀገራት የእስራኤልን ጥቃት ከማውገዝ ባለፈ እንዲቆም በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው
የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት እና የሀገራት የሀይል አሰላለፍ ምን ይመስላል?
ለፍልስጤማዊያን ነጻነት እንደሚታገል የሚገልጸው ሐማስ ከሶስት ሳምንት በፊት በእስራኤል ላይ ያልታሰበ ጥቃት ሰንዝሯል መባሉን ተከትሎ ነበር በአካባቢው ጦርነት የተቀሰቀሰው፡፡
ይህን ተከትሎም እስራኤል የሐማስ ይዞታዎች ናቸው በምትላቸው የጋዛ አካባቢዎች ላይ የአየር ላይ ጥቃቶችን በማካሄድ ላይ ትገኛለች፡፡
ሐማስም በእስራኤል ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት መቀጠሉ ሲገለጽ ሁለቱም ወገኖች ባደረሷቸው ጥቃቶች የተገደሉ ዜጎች ቁጥር በየሰዓቱ እያየለ ይገኛል፡፡
አሜሪካ እስራኤል ለምታደርሰው የመልሶ ማጥቃት በይፋ ድጋፍ እና እቀውቅና የሰጠች ሀገር ስትሆን አሁን ደግሞ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን እና ካናዳ በጋራ ባወጡት መግለጫ ከእስራኤል ጎን እንደሚቆሙ በይፋ ገልጸዋል፡፡
ስድስቱ ሀገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ እስራኤል ራሷን የመከላከል መብት እንዳላት እና ለዚህም ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
የየመን አማጺያን ወደ እስራኤል የሚሳኤል እና ድሮን ጥቃት መፈጸማቸው ተገለጸ
ሀገራቱ አክለውም ሐማስ አግቷቸው የነበሩ ሁለት አሜሪካዊያንን መልቀቁን አድንቀው አሁንም የታገቱ ተጨማሪ ዜጎች እንዲለቀቁ አሳስበዋል ተብሏል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ግን ኢራን፣ኳታር፣ ቱርክ እና ሌሎችም ሀገራት እስራኤል በሐማስ ሰበብ በፍልስጤማዊያን ላይ የጀመረችውን ግድያ እንድታቆም አሳስበዋል፡፡
የኢራን ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ እስራኤል በጋዛ ወታደሮቿን ካሰማራች አካባቢው ወደከፋ ውጥረት እንደሚገባ አስጠንቅቃለች፡፡
ለፍልስጠየማዊያን መንግስት ሰራተኞች እና ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ ታደርጋለች የምትባለው ኳታር በሀማስ የታገቱ ዜጎችን ለማስለቀቅ በማደራደር ላይ ላይ ናትም ተብሏል፡፡
ዶሃ የሀማስ መሪዎችን በማስጠለል እና ሌሎች ድጋፎችን ስታደርግ የቆየች ሲሆን እስራኤል በጋዛ እያደረሰች ያለውን የንጹሃንን ግድያ እንድታቆም በማሳሰብም ላይ እንደምትገኝ ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡
ቱርክ እና ሌሎች ስማቸው ያልተጠቀሱ ሙስሊም ሀገራት ከፍልስጤማዊያን ጎን ከቆሙ ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ሲሆኑ እስራኤል በጋዛ እግረኛ ወታደሮቿን እንዳታስገባ ሲወተውቱ የቆዩ ሀገራትም ናቸው፡፡