የሃማስ ታጣቂዎች ሰሜን ኮሪያ ሰራሽ መሳሪያዎችን ታጥቀዋል?
የደቡብ ኮሪያ የደህንነት ባለሙያዎች ሃማስ የፒዮንግያንግን የጦር መሳሪያዎች እንደሚጠቀም በምርመራ አረጋግጠናል ብለዋል
ሰሜን ኮሪያ በበኩሏ መረጃውን መሰረተ ቢስ እና በአሜሪካ የተቀነባበረ ነው ብላለች
የሃማስ ታጣቂዎች ከ12 ቀናት በፊት በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሲከፍቱ የሰሜን ኮሪያን የጦር መሳሪያዎች መጠቀማቸው ተነገረ።
የቪዲዮ ምስሎችን እና በእስራኤል በውጊያ ላይ የተገኙ መሳሪያዎችን የመረመሩት የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ደህንነት ባለሙያዎች ሃማስ ከሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያዎችን እንደሚያገኝ አረጋግጠናል ብለዋል።
አሶሼትድ ፕረስም አደረግኩት ባለው ማጣራት ሃማስ ሰሜን ኮሪያ ሰራሽ ሮኬት ማስወንጨፊያዎች እና ሌሎች መሳሪያዎችን እንደሚጠቀም ደርሼበታለው ብሏል።
ሃማስ ትከሻ ላይ የሚደረጉና በአንድ ጊዜ አንድ ሮኬት የሚተኩሱ “ኤፍ - 7” መሳሪያዎች ን በስፋት ሲጠቀም እንደሚታይ ነው የተገለጸው።
የሰሜን ኮሪያው “ኤፍ - 7” ከሶቪየት ሰራሹ “አርፒጂ - 7” ጋር እንደሚመሳሰል የሚያነሱት ባለሙያዎች፥ ፒዮንግያንግ ለረጅም ጊዜ የፍልስጤም ታጣቂዎችን ስትደግፍ ቆይታለች ይላሉ።
ሃማስ በሚለቃቸው የቅስቀሳ ምስሎች ላይ ጸረ ታንክ እና ሌሎች ለሽምቅ ውጊያ አመቺ የሆኑ ሰሜን ኮሪያ ሰራሽ መሳሪያዎችን ታጥቆ ስለመታየቱም ያወሳሉ።
በአሁኑ ጦርነትም የሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያዎች በእስራኤል እና በጋዛ ቢታዩ ሊገርም አይገባም ባይ ናቸው።
እስራኤል ስለጉዳዩ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥባለች የሚለው አሶሼትድ ፕረስ ፒዮንግያንግ ሃማስ የጦር መሳሪያዎቿን እየተጠቀመ ነው መባሉን ማስተባበሏል ዘግቧል።
የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ መረጃውን “መሰረተ ቢስ እና ሀሰት ነው፤ አሜሪካ ያቀነባበረችው ተራ ውንጀላ ነው” ብሎታል።
በመንግስታቱ ድርጅት የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማዕቀብ የተጣለባት ሰሜን ኮሪያ በሶሪያ፣ ኢራቅ እና ሊባኖስ የጦር መሳሪያዎቿ በስፋት ጥቅም ላይ ይውላሉ ተብሏል።
በቅርቡም ወደ ሩሲያ የጦር መሳሪያ ልትልክ ትችላለች የሚለው የምዕራባውያኑ ስጋት የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሞስኮ ሲገቡ ይበልጥ መናሩ አይዘነጋም።