4 ሜትር ከሚረዝመው የፑቲንና ማክሮን የውይይት ጠረጴዛ ጀርባ ያለው ሚስጥር ምንድን ነው?
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንና የፈረንሳዩ አቻቸው ኢማኑኤል ማክሮን በሞስኮ ተወያይተዋል
ሁለቱ መሪዎች የተወያዩበት የጠረጴዛ ርዝመት ዙሪያ የክሬምሊን ቤተ መንግስት ማብራሪያ ሰጥቷል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከሰሞኑ በሞስኮ ተገናኝተው በዩክሬን ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል።
ታዲያ በውይይቱ ወቅት መሪዎቹ ከተወያዩበት ጉዳይ ባልተናነሰ በመካከላቸው የነበረው የጠረጴዛ ርቀት በበርካቶች ዘንድ መነጋሪያ ሆኖ ከርሟል።
በሁለቱ መሪዎች መካከል የነበረው ነጭ እና ረጅሙ ጠረጴዛ በበርካቶች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ የከረመ ሲሆን፤ አንዳንዶች ደግሞ ሩሲያ በድብቅ ልታስተላልፍ የፈለገችው ፖለቲካዊ መልእክት ይኖረዋል ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
የሩሲያው ክሬምሊን ቤተ መንግስት በዛሬው እለት የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የፈረንሳዩ አቻቸው ኢማኑኤል ማክሮን በሞስኮ ተቀብለው ባነጋገሩት ወቅት ጠረጴዛው ለምን ረዘመ የሚለው ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል።
ክሬምሊን በማብራሪያውም፤ ፕሬዝዳንት ፑቲን በውይይቱ ወቅት ርቀታቸውን በዚህ መልኩ ያሰፉት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኤል ማክሮን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ለማድረግ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ነው ብሏል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ በፈረንሳይ በኩል አለመረዳቶች ነበሩ፤ ሆኖም ግን እርምጃው የተወሰደው የፕሬዝዳንት ፑቲንን ጤንነት ለመጠበቅ ነው ብለዋል።
ጠረጴዛው በዚህ መልኩ መርዘሙ ምንም አይነት ፖለቲካዊ አለመሆኑን እና በሁለቱ መሪዎች መካከል የነበረው ውይይት ላይ የፈጠረው ጫና እንዳልነበረውም ቃል አቀባዩ አሰስታውቀዋል።