ሀማስ ወደ ጋዛ ሰርግው ከገቡ የእስራኤል ኃይሎች ጋር እየተዋጋሁ ነው አለ ሀማስ ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው በደቡባዊ የጋዛ ግዛት ብረት ለበስ መሳሪያ ከያዘ ጦር ጋር እየተዋጋ ነው
ሀማስ ወደ ጋዛ ሰርግው ከገቡ የእስራኤል ኃይሎች ጋር እየተዋጋሁ ነው አለ።
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ወደ ጋዛ ሰርገው ከገቡ የእስራኤል ኃይሎች ጋር እየተዋጋ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ሀማስ ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው ከካን ዩኒስ ምስራቅ አቅጣጫ በደቡባዊ የጋዛ ግዛት ብረት ለበስ መሳሪያ ከያዘ ጦር ጋር እየተዋጋ ነው።
ሀማስ ይህን ያለው ጋዛን በአየር ያለማቋረጥ እየደበደበች ያለችው እስራኤል በእግረኛ ወታደር አጠቃላይ ጦርነት ትከፍታለች ተብሎ እየተጠበቀ ባለበት ወቅት ነው።
"ታጣቂዎቹ ሰርገው ከገቡት ኃይሎች ጋር ባደረገው ውጊያ ሁለት ቡልዶዘሮችን እና አንድ ታንክ አውድመው ወደ ቦታቸው ተመልሰዋል" ብሏል መግለጫው።
በዚህ ጉዳይ እስራኤል ምላሽ አለመስጠቷን ሮይተርስ ዘግቧል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ በ50 አመታ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ እስራኤል እየወሰደች ያለው የአጸፋ ጥቃት ተጠናክሮ ቀጥሏል።
እስራኤል በሀማስ ይዞታ በሆነችው ጋዛ፣ በሰሜን እስራኤል በኩል ከሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ እና በዌስት ባንክ ባሉ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት እየሰነዘረች ነው።
እስራኤል በአሁኑ ወቅት ጋዛን በመክበብ በእግረኛ ወታደር ለማጥቃት እና የሀማስ ታጣቂዎችን ለመግደል ተዘጋጅታለች።
የአረብ ሀገራት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ ሲያቀርቡ፣አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውን ሀገራት ግን ትኩረታቸውን ሰብአዊ ቀውሱ ላይ ብቻ አድርገዋል።
አሜሪካ ሁለት ግዙፍ የጦር መርከቦች ወደ እስራኤል የባህር ጠረፍ በማስጠጋት ለእስራኤል ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰች ነው።