የማዳጋስካር ፕሬዘዳንት ሁሉንም ሚኒስትሮች ከስራ አገዱ
ማዳጋስካር ከአንድ ወር በፊት የሀገሪቱን ፕሬዘዳንት ለመግደል የተዘጋጀ እቅድ አከሸፍኩ ማለቷ ይታወሳል
የማዳጋስካሩ ፕሬዘዳንት አንድሪ ራጆሊና ሁሉንም የካቢኔ አባላት ከስራ ማገዳቸውን አስታውቀዋል።
የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት አንድሪ ራጆሊና ከአንድ ወር በፊት የውጭ ሀገራት ዜጎች ሳይቀር ተሳትፈውበታል የተባለን የግድያ ሙከራ እቅድ ማክሸፏ ይታወሳል።
በዚህ የግድያ እቅድ ላይ እጃቸው አለበት የተባሉ የጦር ጀነራሎች እና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎችን ጨምሮ ከ21 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጠጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ሲጂተሪኤን አፍሪካ ዘግቧል።
ፕሬዘዳንቱ ሁሉንም ሚኒስትሮቻቸውን ከስራ ማገዳቸው የተገለጸ ሲሆን ለባለስልጣናቱ ከስራ መታገድ እስካሁን ምክንያቱ አልተገለጸም።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ደግሞ ፕሬዘዳንቱ ሚኒስትሮቻቸውን ለምን ከስልጣን አነሱ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “ልክ እንደ እግር ኳስ በመንግስት አወቃቀር ውስጥ ድክመት ሲኖር መቀየር ያለ ነው” ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን ዘገባው ጠቁሟል።
ማዳጋስካር ከአንድ ወር በፊት የነጻነት በዓሏን ባከበረችበት ወቅት የፕሬዘዳንት አንድሪ የቀኝ እጅ በመባል የሚታወቁት ጀነራል ሪቻርድ ራቫሎማናን የመግደል ተሞክሮ እንደከሸፈ ዘገባው አስታውሷል።
የአሁኑ የማዳጋስካር ፕሬዚዳንት አንድሪ ራጆሊና ከሁለት ዓመት በፊት ነበር በምርጫ አሸንፈው ወደ ስልጣን የመጡት።የ44 ዓመቱ ፕሬዚዳንት አንድሪ በፈረንጆቹ 2009 በአገሪቱ ወታደር ታግዚው እስከ ፈረንጆቹ 2014 ድረስ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለውም ነበር።
27 ሚሊዮን ህዝብ ብዛት ያላት ደቡበ አፍሪካዊቷ ሀገር ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት በፈረንጆቹ 1960 ዓመት ነጻነቷን ከተቀዳጀች በኋላ የቀድሞዋ ማላጋሲ ሪፐብሊክ ስሟን ወደ አሁኑ ማዳጋስካር ቀይራለች።