የጣሊያን ማፊያ ቡድን አባላት ላይ የ2 ሺህ 200 ዓመት እስር ተፈረደ
የእስር ቅጣቱ የተላለፈው ከማፊያ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ ከ200 በላይ ሰዎች ላይ ነው
ለ3 ዓመት በተካሄደው የፍርድ ሂደት ከ400 በላይ ጠበቆች እና 900 የሚሆኑ ምስክሮች ቀርበዋል
ከ200 በላይ የጣሊያን የማፍያ ቡድን አባላት በድምር በ2 ሺህ 200 ዓመት የእስር ቅጣት ተፈረደባቸው።
የቅጣት ውሳኔው በደቡባዊ ካላብሪያ ክልል ለሶስት አመት ሲካሄድ ለነበረው የፍርድ ሂደት ፍጻሜ እንዲያገኝ ያደረገ ነው ተብሏል።
በፈረንጆቹ በጥር 2021 በተጀመረው ችሎት ከ400 በላይ ጠበቆች ለተከሳሾቸ ቀርበው የተከራከሩ ሲሆን፤ 900 የሚሆኑ ምስክሮች ቀርበው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ቅጣቱ የተላለፈባቸው ከ200 በላይ ሰዎች 'ንድራንጄታ' ከተባለው የማፊያ ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ቀድሞው የጣሊያን ምክር ቤት አባል የነበሩ ግለሰብ እንዳሉበትም ተነግሯል።
አጠቃላይ የእስር ጊዜ ቅጣቱ ውስጥ አምስት የእድሜ ልክ እስራት እና ሶስት የ30 አመት ቅጣቶችን የሚያካትት ሲሆን፤ ሌሎችም እንደ ተሳትፏቸው የእስር ቅጣቱ ተላልፎባቸዋል።
የፍርድ ሂደቱ የተካሄደው በላሜዚያ ቴርሜ ከሚገኘው የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በልዩ ሁኔታ በተሰራ ከፍተኛ ጥበቃ ባለው ስፍራ ነው የተባለ ሲሆን፤ ስፍራው በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ተከሳሾች የፍርድ ሂደቱን የተከታተሉት በጣሪያ ላይ በተሰቀሉ ስክሪኖች አማካኝነት ነው።
የፍርድ ሂደቱን የመሩት ሶስት ዋና ዳኞችም ለደህንነታቸው ሲባል ለብቻቸው ደህንነቱ የተጠበቀ ቤት ውስጥ እንዲቆዩ መደረጉን እና በፖሊስ ልዩ ጥበቃ ስር መቆየታቸውም ተነግሯል።
የፍርድ ሂደቱ በጥብቅ እና ልዩ ሁኔታ መካሄዱ የማፊያ ቡድኑ በደቡባዊ ጣሊያን ፖለቲካ እና ኅብረተሰብ ላይ ያሳደሩትን ሰፊ ተጽዕኖ የሚያሳይ ነው ተብሏል።
ከተፈረደባቸው ታዋቂ ሰዎች መካከል የቀድሞው የስልቪዮ ቤሩስኮኒ ፓርቲ ፎርዛ ኢጣልያ ጠበቃ እና የቀድሞ ሴናተር የነበሩት ጃንካርሎ ፒቴሊ ይገኙበታል።
በደቡባዊ ጣሊያን ምርመራውን የመሩት ፀረ-ማፊያ አቃቤ ህጎች እንዳሉት የማፊያ ቡድኑ በፕላኔታችን ላይ ካሉት በጣም ኃይለኛ የወንጀል ድርጅቶች አንዱ እንደሆነ እና አሁን በአውሮፓ ውስጥ የኮኬይንን ጨምሮ የሌሎች አደንዛዥ እጾችን ዝውውር በብቸኝነት የሚመራ ድርጅት ነው።
ድርጅቱ በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ ውስጥ መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን በአፍሪካ ውስጥም ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግም ታውቋል።
የጣሊያን አቃቤ ህጎች እንዳረጋገጡት ከሆነ 'ንድራንጄታ' የማፊያ ቡድን አባላት በቅርብ ዓመታት በአውሮፓ፣ በብራዚል እና በሊባኖስ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ንድራንጄታ' የማፊያ ቡድን በዓመት 52 ቢሊዮን ፓውንድ ገቢ አለው ተብሏል።