ጣሊያን ለ30 አመት ስትፈልገው የነበረውን የማፊያ ቡድን መሪ ያዘች
ማቲዮ መሲና ዴናሮ የተባለው የ”ኮሳ ኖስትራ” የማፊያ ቡድን መሪ በሲሲሊ በድብቅ ህክምና ሲከታተል ነው የተያዘው
በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው ዴናሮ በ2002 በሌለበት በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖ ነበር
በጣሊያን ለ30 አመት ሲታደን የነበረው የማፊያ ቡድን መሪ ማቲዮ መሲና ዴናሮ በቁጥጥር ስር ዋለ።
የኮሳ ኖስትራ የማፊያ ቡድን መሪ ነበር የተባለው ዴኔሮ በሲሲሊ መዲና ፓሌርሞ በግል ክሊኒክ በድብቅ ህክምናውን ሲከታተል መያዙን የጣሊያን ፖሊስ አስታውቋል።
ከ100 በላይ የጸጥታ ሃይሎችም ዴኔሮን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተካሄደው ዘመቻ ተሳትፈዋል ነው የተባለው።
ጠቅላይሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒም የዴናሮን መያዝ “ታላቅ ድል ነው” ያሉት ሲሆን፥ በቁጥጥር ስር ላዋሉት የጸጥታ ሃይሎች አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ማቲዮ መሲና ዴናሮ በፈረንጆቹ በ1993 በሚላን ለተፈጸመው የቦምብ ጥቃትና በፍሎረንስ እና ሮም በርካቶችን ለህልፈት ለዳረጉ ጥቃቶች ተጠያቂ የሚደረገውን የማፊያ ቡድን ሲመራ መቆየቱ ይነገራል።
የሚመራው የማፊያ ቡድን “ኮሳ ኖስታራ” በህገወጥ የገንዘብ እና የአደንዛዥ እጽ ዝውውር ወንጀሎች የተዘፈቀ ስለመሆኑም ይነሳል።
ስለዚሁ የማፊያ ቡድን መረጃ ያላቸውን ሰው የ12 አመት ታዳጊ በመጥለፍም ለሁለት አመት ካቆዩት በኋላ በአሲድ በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸውን የጣሊያን አቃቢያነ ህግ ይገልጻሉ።
መሲና ዴናሮ ከፈረንጆቹ 1993 ጀምሮ በጣሊያን ፖሊስ ሲፈለግ ቢቆይም ደምዛውን አጥፍቶ ቆይቷል።
በ2013 እህቱ ፓትሪዚያ እና ሌሎች ባልደረቦቹ በቁጥጥር ስር ውለው ከግለሰቡ ጋር ግንኙነት ያላቸው የቢዝነስ ተቋማት ቢደረስባቸውም የማፊያ ቡድኑን መሪ ግን መያዝ ሳይቻል ቀርቷል።
በዛሬው እለት በፓሌርሞ የተያዘው ዴናሮ በ2002 በሌለበት በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖ እንደነበር ሬውተርስ በዘገባው አስታውሷል።