በጣሊያን አንድ ግለሰብ በከፈተው የተኩስ የጠቅላይ ሚኒስትሯን ጓደኛ ጨምሮ ሶስት ሴቶች ተገደሉ
ተጠርጣሪው “ሁላችሁንም እገድላችኋለሁ” እያለ ሲዝት እንደነበር የ ዓይን እማኞች ተናግረዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ጆዮርጂያ ሜሎኒ በድርጊቱ ማዘናቸው ገልጸዋል
በጣሊያን አንድ ግለሰብ በከፈተው የተኩስ እሩምታ ሶስት ሴቶች ተገደሉ፡፡
ከተገደሉት ሴቶች አንዷ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆዮርጂያ ሜሎኒ የልብ ጓደኛ መሆኗም ነው የጣሊያን ፖሊስ የተገለጸው፡፡
ከሟቾች ሌላ ሁለት ሌሎች ሴቶች እና ሁለት ወንዶች የቆሰሉ ሲሆን አንደኛው ለህይወቱ አስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡
የ57 ዓመት ጎልማሳ ጥቃቱን ለምን እንደፈጸመ በግልጽ የተባለ ነገር ባይኖርም፤የአካባቢ የነዋሪዎች ኮሚቴ አባላት ከነበሩት ሶስት ሴቶች ጋር አምባጓሮ ፈጥሮ እንደነበር የፖሊስ መረጃ ያመለክታል፡፡
ተጠርጣሪው ከቤት ሊያባሩኝ ይፈልጋሉ የሚል ቅሬት እንደነበረውና በዚህም “ሁላችሁንም እገድላችኋለሁ” እያለ ሲዝት እንደነበር ሮይተርስ የዓይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።
እንዳለውም እሁድ እለት በተጠራው ኮሚቴ ስብሰባ ላይ በሽጉጥ የተኩስ እሩምታ ከፍቶ ገድሏቸዋል ብለዋል የዓይን እማኞቹ፡፡
ድርጊቱን ተከትሎ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ተረባርበው ግለሰቡን በቁጥጥር ስር እንዳዋሉትም ጭምር ተናግረዋል፡፡
የአፓርትመንቱ ኮሚቴ ገንዘብ ያዥ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩትና የ10 ዓመት ልጅ እናት ኒኮሌታ ጎሊሳኖ በደረሰባቸው ጉዳት ከሞቱት 3 ሴቶች መካከል አንዷ ናቸው።
የሮም ከንቲባ ሮቤርቶ ጓልቴሪ አሳዛኙን ድርጊት “ጭካኔ የተሞላበት” ሲሉ አውግዘውታል።
ኒኮሌታ በመባል የምታወቀው የልብ ጓደኛቸው ያጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ጆዮርጂያ ሜሎኒ በበኩላቸው ወዳጃቸውን በማጣታቸው የተሰማቸውን ሐዘን ከገለጹ በኋላ “እሷ ሁልጊዜም ቆንጆና ደስተኛ ሴት ነበረች” ሲሉ ተናግረዋል።
“ኒኮሌታ ልጆቿን ተንከባካቢ እናት፣ ልበ ቀና እና ሚስጥረኛ ጠንካራ ነገር ግን ሆደ ቡቡ ሴት ነበረች"ም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሯ ባሰፈሩት ማስታወሻ።