ሃሪ ማጓየር የህዳር ወር የፕሪሚየር ሊጉ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን ወሰደ
ሆላንዳዊው የዩናይትድ አሰልጣን ኤሪክ ቴን ሃግም የወሩ ምርጥ አሰልጣኝ ተብሎ ተመርጧል
ቀያዮቹ ሰይጣኖች በህዳር ወር በሶስት ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርባቸው ማሸነፋቸው ይታወሳል
የማንቸስተር ዩናይትዱ ተከላካይ ሃሪ ማጓየር የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የህዳር ወር ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን ወሰደ።
የክለቡ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግም የወሩ ምርጥ አሰልጣኝ ተብሎ ተመርጧል።
ማንቸስተር ዩናይትድ በህዳር ወር ያስመዘገበው ውጤት ማጓየርና ቴን ሀግ ሽልማቱን እንዲወስዱ አድርጓል።
በክረምቱ ዝውውር ኦልትራፎርድን ለመልቀቅ ተቃርቦ የነበረው እንግሊዛዊ የዩናይትድ የኋላ መስመር ደጀንነቱን አስመስክሯል።
ክለቡ በህዳር ወር ፉልሃም፣ ሉተን እና ኤቨርተንን ሲያሸንፍም ምንም ግል አልተቆጠረበትም።
የ30 አመቱ ተከላካይ ከማንቸስተር ሲቲው ጀርሚ ዶኩ፣ ከኒውካስትል ዩናይትዱ አንቶኒ ጎርደን እና ከቼልሲው ራሄም ስተርሊንግ ጋር ተፎካክሮም የወሩ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን መውሰድ ችሏል።
ማጓየር በኢንስታግራም ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክትም ለክለቡ ደጋፊዎች እና ለአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ምስጋናውን አቅርቧል።
በሰባት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ውስጥ አምስቱን ያሸነፈውየኤሪክ ቴን ሀግ ቡድን በ27 ነጥብ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ስድስተኛ ላይ ተቀምጧል።
አጀማመሩ ጥሩ ያልነበረው ዩናይትድ ከአምናው ሻምፒዮንና የከተማ ተቀናቃኙ ሲቲ ያለውን የነጥብ ልዩነትም ወደ ሶስት ማጥበብ ችሏል።