ኦናና ዩናይትድ በሙኒክ ለደረሰበት ሽንፈት ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ገለጸ
በኦልትራፎርድ ጅማሮው ያላማረው ካሜሮናዊው ግብ ጠባቂ ከአሊያንዝ አሬናው ሽንፈት በኋላ አስተያየቱን ሰጥቷል
አሰልጣኝ ቴን ሃግ በበኩላቸው ኦናና ስህተቱን ማመኑ ጥሩ ቢሆንም ችግሩ እንደቡድን የሚወሰድ ነው ብለዋል
የማንቸስተር ዩናይትዱ ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና ለትናንት ምሽቱ የአሊያንዝ አሬና ሽንፈት ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ገለጸ።
ኦናና ከቲኤንቲ ስፖርት ጋር ባደረገው ቆይታ፥ “በእኔ ስህተት ምክንያት ማሸነፍ አልቻልንም፤ አጀማመራችን ጥሩ ቢሆንም ስህተት ሰርቼ ጎል ከተቆጠረ በኋላ የኳስ ቁጥጥራችን ቀንሷል፤ ለዚህም ተጠያቂው እኔ ነኝ” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
ከኢንተርሚላን በ47 ሚሊየን ፓውንድ ቀያዮቹ ሰይጣኖችን የተቀላቀለው ኦናና በኦልትራፎርድ ጅማሮው ጥሩ እንዳልሆነም ገልጿል።
ይሁን እንጂ እንደ ቡድን በጋራ በመስራትና ከስህተቱ በመማር ደጋፊዎችን ለመካስ ዝግጁ መሆኑን ነው የ27 አመቱ ግብ ጠባቂ የተናገረው።
አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ በበኩላቸው ኦናና ስህተቱን ማመኑ መልካም ቢሆንም ለሽንፈቱ ሃላፊነቱን የሚወስደው ጠቅላላ ቡድኑ ነው ብለዋል።
“በእግርኳስ ስህተት የማይሰራ የለም፤ ኦናና የመጀመሪያዋ ጎል ላይ ቢሳሳትም በሁለተኛው አጋማሽ ያዳናዳቸው ሙከራዎች ዳግም ለድል እንድንቃረብ አድርገውናል” ሲሉም በግብ ጠባቂው ላይ የሚነሱ ትችቶችን እንደቡድን እንዲወሰዱ አሳስበዋል።
የቀድሞው የዩናይትድ ተከላካይ ሬዮ ፈርዲናንድም እንደ ቴን ሃግ ሁሉ ኦናና ወደ ሚዲያ በመምጣት ሃላፊነት እወስዳለሁ ብሎ አስተያየት መስጠቱን አድንቋል።
ዩናይትድ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች 14 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ከ1958 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሶስት እና ከዚያ በላይ ጎሎችን በማስተናገድም ደካማ አጀማመር እያሳየ ነው።