የማንቸስተር ዩናይትድ ዋጋ በ740 ሚሊየን ዶላር ዝቅ ማለቱ ተነገረ
የግሌዘር ቤተሰቦች ዩናይትድን እንደማይሸጡ ከገለጹ በኋላ የክለቡ የአክሲዮን ዋጋ በዚህ ሳምንት በ19 በመቶ መውረዱ ተገልጿል
የክለቡ ደጋፊዎች በአሜሪካውያኑ ባለሃብቶች ላይ ግፊት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል
የማንቸስተር ዩናይትድ የአክሲዮን ዋጋ በዚህ ሳምንት ብቻ በ19 በመቶ መውረዱ ተነገረ።
የአክሲዮን ዋጋው መውረዱ የክለቡን ዋጋ በ740 ሚሊየን ዶላር እንዲቀንስ አድርጎታል፤ ይህም የክለቡን ዋጋ ወደ 3 ነጥብ 15 ቢሊየን ዶላር ዝቅ የሚያደርገው ነው።
ከፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ በኣአክሲዮን ገበያ ላይ መሳተፍ የጀመረው የእንግሊዙ ክለብ በ11 አመታት ውስጥ የአክሲዮን ዋጋው በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን ሲኤንኤን ዘግቧል።
ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የግሌዘር ቤተሰቦች ዩናይትድን ለጊዜውም ቢሆን የመሸጥ ፍላጎት የላቸውም የሚል ዘገባን ዴይሊ ሜል ይዞ መውጣቱ ነው።
የዩናይትድ ባለቤቶች በህዳር ወር 2023 ክለቡን ለመሸጥ ማሰባቸውን ካሳወቁ በኋላ ብሪታንያዊው ቢሊየነር ጂም ራትክሊፍ እና የኳታሩ ሼክ ጃስሚን ቢን ሃማዳ አልታኒ ፉክክሩን መቀላቀላቸው ይታወሳል።
የግሌዘር ቤተሰቦች ግን የግዥ ጥያቄ ላቀረቡት ባለሃብቶች ጋር መስማማት አልቻሉም።
ክለቡን ለመሸጥ ያቀረቡት የተጋነነ የ10 ቢሊየን ፓውንድ ዋጋ ከሁለቱ ባለሃብቶች ጋር ሳያቀራርባቸው መቅረቱ ተነግሯል።
እናም ዩናይትድን እስከ 2025 አቆይተው በርካታ ተጫራቾችን በማሳተፍ በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ ስለማሰባቸው የዴይሊ ሜል ዘገባ አመላክቷል።
በመላው አለም 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ደጋፊ እንዳለው የሚነገርለትን ማንቸስተር ዩናይትድ በፈረንጆቹ 2005 የገዙት የግሌዘር ቤተሰቦች ክለቡን እንዲሸጡ የሚደረገው ግፊት ግን ቀጥሏል።
ከ2017 ወዲህ ከዋንጫ የራቀው ክለቡ አሁን በፕሪሚየር ሊጉ 11ኛ ደረጃን ይዟል።
በ18 አመት ውስጥ ከክለቡ ደጋፊዎች ጋር ፊት ለፊት ያልተገናኙት የግሌዘር ቤተሰቦች ታላቁን ክለብ ቁልቁለት ውስጥ እየከቱት ነው ያሉ ደጋፊዎች የተቃውሞ ሰልፎችን ለማድረግ እየተዘጋጁ ነው ተብሏል።
ጋሪ ኔቭልን ጨምሮ በርካታ የክለቡ የቀድሞ ተጫዋችም ተቃውሞውን ተቀላቅለዋል።