ከሮና ቫይረስ እና የተፈጥሮ አደጋዎች በ2020 ኢትዮጵያ የተፈተነችባቸው ዋነኛ ማህበራዊ ክስተቶች ናቸው
በተጠናቀቀው የአውሮፓውያኑ 2020 ኢትዮጵያ እጅግ ፈታኝ ወቅቶችን አሳልፋለች፡፡ በዓመቱ ከተስተናገዱ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው፡ የሕዳሴ ግድብ ፈታኝ ድርድሮች እና የዉሃ ሙሌት፣ የትግራይ ክልል ቀውስ ፣ የንጹሃን ግድያ እና መሰል ጉዳዮች በተጨማሪ ኢትዮጵያ በማህበራዊ ክስተቶችም ተፈትናለች፡፡ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችንም ካስከተሉት ማህበራዊ ክስተቶች መካከል ደግሞ ኮሮና ቫይረስ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ የተፈጥሮ አደጋዎችም የተስተዋሉ ሲሆን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ደግሞ በአንድ ዓመት ልዩነት 2ኛውን ሳተላይት አምጥቃለች፡፡
1/ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ተጽዕኖው
በታህሳስ ወር በቻይና ዉሀን ከተማ የተከሰተው ዓለም እንደ አዲስ የተዋወቀችው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) መላውን ዓለም ለማዳረስ ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ ኢትዮጵያም ቫይረሱ ከተከሰተ 4 ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መጋቢት 14 የመጀመሪያውን የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ አገኘች፡፡
በወቅቱ በአንድ ጃፓናዊ ላይ የተገኘው ይህ ቫይረስ አንድ ሁለት እያለ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ከ 123 ሺ በላይ ሰዎችን አጥቅቷል፡፡ ከ 1 ሺ 900 በላይ ሰዎችም ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡
ቫይረሱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም ተመሳሳይ ሊባል የሚችል ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ በርካቶችን ከስራ ገበታቸው አፈናቅሏል ፤ በህዝብና በመንግስት ላይ ከፍተኛ የማህበረ ኢኮኖሚ ቀውስ አስከትሏል፡፡ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት በሚል ኢትዮጵያ 5 ወራትን በአስቸኳይ ጊዜ ዉስጥ ስታሳልፍ ፣ የስራ ሰዓት ሽግሽግ ተደርጓል ፤ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል ፤ የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እና ሁሉም ስፖርታዊ ዉድድሮች ተቋርጠዋል፡፡በተለያዩ ሀገራት በዋናነት ኢኮኖሚያዊ ቀውስን ተከትሎ የተለያዩ ፖለቲካዊ ቀውሶችም ተከስተዋል፡፡
2/ የተፈጥሮ አደጋዎች በኢትዮጵያ
2.1 የጎርፍ አደጋ
በኢትዮጵያ በተለይ በነሀሴ ወር የጣለው ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በተለያዩ አካባቢዎች በርካቶችን ለጉዳት ዳርጓል፡፡ በአፋር ክልል ሁሉም ዞኖች፤ በአማራ ክልል፡ ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ጎንደር ፣ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን እናደቡብ ወሎ፤ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና በሌሎችም የክልሉ ዞኖች ፣በጋምቤላ አኙዋክና ኑዌር ዞኖች እንዲሁም በሱማሌ ክልል ሽንሌ ዞን በጎርፍ የተጠቁ አካባቢዎች ናቸው፡፡ በተለይ በአፋር፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በዜጎች ላይ የሞትና የመፈናቀል አደጋ ማስከተሉ ይታወሳል፡፡ በደቡብ ክልል ጋሞ እና ጎፋ ዞኖችን ጨምሮ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ደግሞ በተለይ የመሬት ናዳ የብዙዎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡
ባለፈው የክረምት ወቅት ብቻ 1 ሚሊዮን 17ሺ 854 ዜጎች ለጉዳት ሲዳረጉ ከነዚህ ውስጥ 292 ሺ 863 ዜጎች ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የጎርፍ አደጋዎችን ለመከላከል የመከላከያ ሠራዊት አባላት ተሳትፎ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡
2.2 የበረሃ አንበጣ መንጋ
የበረሃ አንበጣ መንጋ አርሰው በሚበሉና በሚያበሉ ኢትዮጵያውያን ላይ ከፍተኛ ቀውስ ፈጥሯል፡፡
የአንበጣ መንጋው በተለያዩ ክልሎች የአርሶ አደሩን የሰብልና የቋሚ ተክል ዝሪቶች ያወደመ ሲሆን በርካቶችንም ላልተጠበቀ ችግርና ዱብዳ ዳርጓቸዋል። ለአብነትም በደቡብ ወሎ ብቻ በአጠቃላይ 54ሺ 997 የቤተሰብ አባላት ያሏቸው 9ሺ 759 አባወራና እማወራ አርሶ አደሮች ሰብላቸው ተጎድቷል፡፡
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ያጋጠውን አንበጣ መንጋ ለመከላከል የአውሮፕላን ኬሚካል እርጭት ሲካሄድ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን ይህንኑ ስራ በመስራት ላይ የነበረች አውሮፕላን በወረባቦ ወረዳ ከተከሰተች ከቀናት በኋላ ሁለተኛዋ ደግሞ በሀረርጌ መከስከሷ ይታወሳል፡፡
የተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2020 ከላይ የተጠቀሱትን ዋና ዋና ክስተቶች ጨምሮ በርካታ አስከፊም አስደሳችም ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ክስተቶች የተስተናገዱበት ዓመት ሆኖ አልፏል፡፡ የ10 ሰዎች ህይወት ያለፈበት በጎንደር የጥምቀት በዓል ላይ የደረሰው አደጋ በዓመቱ ከተስተዋሉ በርካታ ክስተቶች መካከል ይገኝበታል፡፡ ቀጣዩ የ2021 ዓመት በኢትዮጵያ ቸር ወሬዎች የሚሰሙበት እንዲሆን አል ዐይን ምኞቱን ይገልጻል፡፡
3/ ኢትዮጵያ ያመጠቀቻት ሁለተኛ ሳተላይት
2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን ሳተላይት ማምጠቋ ይታወሳል፡፡ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ከቤጂንግ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የቻይና ጠፈር ምርምር ማዕከል የመጠቀችው ETRSS-1 የሚል ስያሜ የተሰጣት ሳተላይቷ የታሰበላትን ቦታ ይዛ ስራዋን በአግባቡ እየሰራች ስለመሆኑ መገለጹ የሚታወስ ነው፡፡ ሳተላይቷ በቀን አስራ አራት ጊዜ በተዘጋጀላት ምህዋር እየዞረች መረጃ የምትሰበስብ ሲሆን በቀን አራት ጊዜ ደግሞ የሰበሰበችውን መረጃ የመቀበል ስራ ይሰራል፡፡ የመጀመሪያዋ ሳተላይት ከመጠቀች ከዓመት በኋላ ኢትዮጵያ ሁለተኛዋን ሳታላይት ማምጠቋን ይፋ አድርጋለች፡፡ የሪሞት ሴንሲንግ ሳተላይቷ ET-SMART-RSS በስኬት መምጠቋንም የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በማህበራዊ ገጹ አስታውቋል፡፡
4/ በኢትዮጵያ የታየው የፀሐይ ግርዶሽ
እሁድ ሰኔ 14 ቀን 2012 ዓ.ም በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ፀሐይ ከ60 እስከ 99 በመቶ ተሸፍና ከከፊል ቀለበታማ ግርዶሽ ታይቷል፡፡
በሌሎች አንዳንድ የዓለማችን ክፍሎችም በዕለቱ የፀሀይ ግርዶሽ ታይቶ የነበረ ቢሆንም ግርዶሹን በሙላት ለማየት እንደኢትዮጵያ አመቺ ስፍራ እንዳልነበረ የዘርፉ ተመራማሪዎች ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በኋላ በዓለም የፀሐይ ግርዶሽን ለማየት 18 ዓመታትን እንደሚወስድ የዘርፉ ባለሙያ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ደግሞ የአሁኑን አይነት የፀሐይ ግርዶሽ ለማየት ከ140 በላይ ዓመታትን መጠበቅ ግድ ይላል፡፡