በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሞት ምጣኔ 1.52 በመቶ መሆኑ ተገለጸ
በቫይረሱ ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች መካከል 51.9 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ ነው
በኢትዮጵያ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ቫይረሱ መከሰቱን የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሞት ምጣኔ 1.52 በመቶ መሆኑ ተገለጸ
በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተይዘው ለህልፈት የሚበቁ ሰዎች ምጣኔ 1.52 በመቶ መሆኑን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተሩ አስቻለው አባይነህ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት እስካሁን በኢትዮጵያ በቫይረሱ ከሚያዙት 57 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ15-34 ሲሆን ከሟቾች ውስጥ ደግሞ 51.9 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ ነው።
በቫይረሱ የሞት ምጣኔ በኢትዮጵያ 1.52 በመቶ ፣ በአፍሪካ 2.4 በመቶ ፣ በዓለም ደግሞ 2.8 በመቶ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተይዘው የሚገኙ ሰዎች ውስጥ 63 በመቶው ምልክት የማያሳዩ እንደሆኑም ታውቋል። ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ከሐምሌ እና ነሐሴ በላይ አሁን ላይ ወደ ፅኑ ሕሙማን የሚገቡ ታማሚዎች ብዛት እየጨመረ እንደመጣም ነው የገለጹት፡፡ 1.4 በመቶ የሚሆኑት በሆስፒታል የሚገኙ ታማሚዎች በፅኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ምክትል ዳይሬክተሩ እንዳሉት በኢትዮጵያ ሁሉም ወረዳዎች ቢያንስ አንድ በኮቪድ የተያዘ ሰው ሪፖርት አድርገዋል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ ፣ ኦሮሚያ ክልል ፣ ትግራይ ክልል ፣ አማራ ክልል ፣ ደቡብ ክልል እና ሲዳማ ክልል በቅደም ተከተል ከፍተኛ የቫይረሱ ተጠቂዎች የተገኙባቸው ስለመሆኑም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
ርቀትን ሳይጠብቁና ማስክ ሳያደርጉ አገልግሎት መቀበልም ሆነ መስጠት ለቫይረሱ ተጋላጭነትን ስለሚጨምር ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አሳስበዋል፡፡ ቸልተኝነት እና መዘናጋት አሁንም በሰፊው እንደሚስተዋል በመግለጽ ይህ ዋጋ ስለሚያስከፍል ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል በቫይረሱ ሊያዝ ስለሚችል ጤናውን ከመጠበቅ ሊዘናጋ እንደማይገባም ነው ሚኒስትሯ ያስጠነቀቁት፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያተወካይ ባውሬማ ሀማ ሳምቦ ፣ የህክምና ባለሙያዎች እና የኢትዮጵያ መንግስት ቫይረሱን ለመከላከል ያደረጉትን ጠንካራ ጥረት እና ቁርጠኛ አመራር አድንቀዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋልም ነው ያሉት ተወካዩ፡፡ ርቀትን መጠበቅ፣ እጅን መታጠብ፣ በትምህርት ቤቶች መሰባሰብን የሚጠይቁ ሁነቶችን መሰረዝ የሚመከሩ ናቸው ብለዋል የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ፡፡
በኢትዮጵያ እስከ ትናንት ጥቅምት 09 ቀን 2013 ዓ.ም የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 89,860 ሲሆን ከነዚህም 43,149 ሰዎች ያገገሙ ሲሆን የ1,365 ሰዎች ህይወት ማለፉን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡ አሁን ላይ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር 45,344 ነው፡፡