የትግራይ ክልል ቀውስ እና የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትን ጨምሮ በዓመቱ በርካታ ሁነቶች ተስተናግደዋል
የተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2020 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተለያዩ ሁነቶች ተስተውለዋል፡፡ በሀገሪቱ ከተከሰቱ ዐበይት ሁነቶች ደግሞ የህዳሴ ግድብ የዉሃ ሙሌት ፣ በትግራይ ክልል የተካሄደውና እየተካሄደ ያለው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ፣ የንጹሀን ግድያና መፈናቀልእና ሌሎችም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትርጉም ያላቸው ክስተቶች አልፈዋል፡፡ እነዚህ ክስተቶች በአወንታዊነትም በአሉታዊነትም ቢነሱም ፣ ብዙዎቹ ግን ሀገሪቱን ዋጋ አስከፍለዋል ፤ በማስከፈልም ላይ ናቸው፡፡
በዓመቱ ውስጥ የተከሰቱ ዋና ዋና ፖለቲካዊ ክስተቶችን በአጭሩ ተመልክተናል፡፡
1/ የሕዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል ድርድሮች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ በተለየ ሁኔታ የሦስትዮሽ ድርድሩ ባለፈው ዓመት ጠንከር ብሎ ተስተውሎ ነበር፡፡ የዚህ ምክንያቱ አሜሪካና የዓለም ባንክ በድርድሩ ውስጥ በአሸማጋይነት መግባታቸው ሲሆን ወደኋላ ላይ ግን ጉዳዩን የአፍሪካ ሕብረት እየተመለከተው ነው፡፡ ሐምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የመነጋገሪያ አጀንዳ አድርጎት ቆይቷል፡፡ በክረምቱ ኢትዮጵያ በግድቡ4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መያዟን አስታውቃለች፡፡ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ብትጀምርም ግብጽና ሱዳን እንደፈሩት ጉልህ ጉዳት አለማድረሱ መረጋገጡን ገልጻለች፡፡ የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መከናወኑ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ብስራት ነው፡፡
2/ የምርጫ መራዘም እና “የትግራይ ክልላዊ ምርጫ”
የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ በ 2012 ሊደረግ የነበረውን ሀገር አቀፍ ምርጫ እንዲራዘም አድርጓል፡፡ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ሊደረግ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ምርጫ ፣በኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ምክንያት፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አማካኝነትእንዲራዘም ተወስኗል፡፡
ምርጫው በ2012 መካሄድ አለበት የሚል ሃሳብ የነበረው ሕወሓት በውሳኔው ከፍተኛ ተቃውሞ አቅርቦ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት በትግራይ ክልል ምርጫ አደርጋለሁ የሚል መግለጫ መስጠቱና በክልሉ ምርጫ ኮሚሽን እንዲቋቋም ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ከምርጫው ጋር በተያያዘ የተፈጠረው አለመግባባት ተካርሮ የትግራይ ክልል በተናጠል ምርጫ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቆ ጳጉሜ 4 ቀን 2012 ዓ.ም ክልላዊ ምርጫ አድርጓል፡፡
የትግራይ ምርጫ ከመካሔዱ ከ4 ቀናት በፊት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ፣ በክልሉ የሚደረገው ምርጫ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር መሆኑን በመግለጽ ምርጫው ቢደረግም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(1) መሰረት እንዳልተደረገ እንደሚቆጠር እና ተቀባይነት እንደማይኖረው ውሳኔ አሳለፈ፡፡ በምርጫው ምክንያት የትግራይ ክልል እና የፌዴራሉ መንግስት ፍጥጫ ይበልጥ እየተካረረ መምጣቱ የሀገሪቱን ፖለቲካዊ መጻኢ ዕድል ፈንታ ለብዙ ትንታኔዎች አጋልጧል፡፡ ነገሮች ወደ መጨረሻው ጫፍ ደርሶ፣ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር መከለከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን የፌዴራል መንግስት ይፋ አደረገ፡፡
3/ የሕግ ማስከበር ዘመቻ በትግራይ ክልል
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፣ ሕወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገልጸው በትግራይ ክልል ሕግ የማስከበር ዘመቻ እንዲጀምር ትዕዛዝ መስጠታቸውን በውድቅት ለሊት አስታወቁ፡፡
ቦሦስት ምዕራፎች ተከፍሎ በተካሄደው ዘመቻ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሕዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም መቐሌን መቆጣጠሩ ተሰማ፡፡ በዚሁ የሕግ ማስከበር ሥራ በቀጣይነት በሕግ የሚፈለጉ የሕወሓት አመራሮችና ከመከላከያ የከዱ አባላትና አመራሮችን የመያዝ ስራ እየተሰራ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ እስካሁንም የቀድሞው የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳድር አምባሳደር አዲስ ዓለም ባለማ (ዶ/ር) ፣ የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ ኬሪያ ኢብራሂም እና በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር አድርገዋል የተባሉ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች መያዛቸው ይታወሳል፡፡ የሀገር መከለከያ ሚኒስቴር የሕወሓት አመራሮች ያሉበትን ቦታ ለጠቆመ ግለሰብ 10 ሚሊዮን ብር እንደሚሸልም ገልጿል፡፡
በሕግ ማስከበር ዘመቻው ከ50 ሺ በላይ ዜጎች ወደ ሱዳን የተሰደዱ ሲሆን ሌሎች በርካታ ሰዎች በሀገር ውስጥ ተፈናቅለዋል፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በትግራይ በተካሄደውን የሕግ ማስከበር ሥራ በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶችንሰጥቷል፡፡ በአንድ ወገን ድርድር ይደረግ ያሉ ሲኖሩ በሌላ በኩል ደግሞ የሉዓላዊነትና ግዛታዊ አንድነትን የማስጠበቅ ዘመቻ ነው፤ ቶሎ መጠናቀቅ አለበት የሚሉ ተስተውለዋል፡፡ የሕግ መስከበር ሥራው ከተጀመረ አምስት ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ የአፍሪካ ሕብረትና የምስራቅ አፍሪከ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ኢትዮጵያ ላከናወነችው የሕግ ዘመቻ ዕውቅና መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
4/ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ እና መዘዙ
በአውሮፓውያኑ 2020 ኢትዮጵያ ካስተናገደቻቸው አሳዛኝ ክስተቶች ባለፈው ሰኔ ወር የተፈጠረው የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ እና ይህን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማና በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው የበርካታ ንጹሀን ሰዎች መገደል አንዱ ነው፡፡
ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም አዲስ አበባ ገላን አካባቢ ምሽት 3 ሰዓት ገደማ በግል ተሸከርካሪው ውስጥ እያለ በተተኮሰበት ጥይት ነበር ዝነኛው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ የተገደለው፡፡ የአርቲስቱ ሞት በብዙ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ቁጣን ቀስቅሶ በርካታ ንጹሀን ዜጎች ያለሀጢያታቸው እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል፡፡ በተለይም በምዕራብ አርሲ ፣ በሀረርጌ እና በአዲስ አበባ በተፈጸመው ጥቃት ቢያንስ 229 ሰዎች መሞታቸውን መንግስት መግለጹ ይታወሳል፡፡ በርካታ የንግድና የመኖሪያ ቤቶች ፣ ተሸከርካሪዎች እና የተለያዩ ንብረቶችም ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ወድመዋል፡፡ የሀጫሉን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ሁከት ከተፈጠረው እልቂት ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ በርካታ ፖለቲከኞች እና የሚዲያ ሰዎችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል፡፡
ይህ ክስተት በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ እንዲቆይም ምክንያት ሆኗል፡፡ የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ለ15 ቀናት የሞባይል ደግሞ ለ23 ቀናት ተዘግተው ከቆዩ በኋላ ነው የተለቀቁት፡፡
5/ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የንጹሃን ግድያዎች
በተጠናቀቀው በአውሮፓውያኑ 2020 በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በእርስበርስ ግጭት እና በጅምላ ጭፍጨፋ በርካታ ንጹኃን ህይወታቸውን አጥተወል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመለክተው ፣ በማይካድራ ሳምሪ በተባሉ ወጣቶች ቡድን እና በትግራይ ክልል የጸጥታ ኃይሎች ቅንጅት የተፈጸመው ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ ሀገሪቱ ካስተናገደቻቸው የንጹሃን ግድያዎች ወደር የማይገኝለት ነው፡፡
መከላከያ ሠራዊት በክልሉ ባከናወነው የሕግ ማስከበር እርምጃ ፣ ማይካድራን ከተቆጣጠረ በኋላ ከ700 በላይ ንጹሃን ሰዎች በማንነታቸው ብቻ በአሰቃቂ መንገድ ተገድለው መገኘታቸው ይታወቃል፡፡ የተለያዩ የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸው ደግሞ የሟቾቹን ቁጥር ከሚጠበቀው በላይ ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ተሰግቷል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተለያዩ ቦታዎች ላይ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ተፈጽመዋል፡፡ በዚህም ጥቃት በርካታ ንጹሃን ህይወታቸውን ሲያጡ ፣ ብዙዎች ቆስለዋል ፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የብዙዎች ቤት የተቃጠለ ሲሆን ሰብሎቻቸውም በእሳት ጋይተዋል፡፡ ታህሣሥ 13 ብቻ በቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ በጉሙዝ ሽፍታዎች የተገደሉ ንጹሃን ቁጥር 207 መድረሱን ኢሰመኮ ይፋ አድርጓል፡፡
በወለጋ የተለያዩ አካባቢዎችም የብዙዎች ሕይወት በማንነታቸው ብቻ ተቀጭቷል፡፡ ምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ለስብሰባ ተብለው የተጠሩ ንጹሃንን በጅምላ የጨፈጨፉበት አጋጣሚም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ኮሚሽኑ በደቡብ ክልል ሰገን አካባቢም በተፈጠሩ ግጭቶች 66 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን አስታውቋል፡፡ የንጹሃን ሞት ለወሬ እስኪሰለች በተፈጸመበት 2020 ፣ በደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳ ፣ በምዕራብ ጉጂ ፣ በአፋር እና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች እንዲሁም በሌሎችም የተለያዩ ስፍራዎች ብዙዎች በግፍ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
6/ የኢትዮ ሱዳን የድንበር ውዝግብ
ለረዥም ዓመታት በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል የነበረው የድንበር ውዝግብ ካለፈው ወር ጀምሮ ከፍተኛ ውጥረት ላይ ደርሷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ስራ ከጀመረ ከ 6 ቀናት በኋላ የሱዳን ጦር በኢትዮጵያ ላይ በከባድ መሳሪያ በመታጀብ ወረራ መፈጸሙን ም/ጠ/ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገልጸዋል፡፡ ሱዳን በበኩሏ ፣ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ሚሊሻዎች ጥቃት ፈጽመውብኛል ብትልም ፣ በኢትዮጵያ ተይዞብኛል ያለችውን ሰፊ ቦታ በኃይል መቆጣጠሯን አስታውቃለች፡፡
ሁለቱ ሀገራት የድንበር ጉዳዮችን በውይይት ለመፍታት ጥረት ቢያደርጉም እስካሁን ተጨባጭ ውጤት አላመጣም፡፡ በአሁኑ ወቅት ሱዳን ከፍተኛ ጦር ድንበር ላይ ማስፈሯን ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት ላለፉት 25 ዓመታት ከነበረው በላይ ውጥረት ውስጥ ገብተዋል፡፡
7/ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ
የተጠናቀቀው የአውሮፓውያኑ 2020 በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በፌደራል ስርዓት ውስጥ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት በህዝበ ውሳኔ አዲስ ክልል የተመሰረተበት ዓመትም ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔን በህዳር 2019 አስፈጽሞ በዚያው ወር የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት ያሳወቀ ሲሆን የመጨረሻ ውጤቱን ደግሞ ሕዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም/በአውሮፓውያኑ ታህሣሥ 2019 አሳውቋል፡፡ በዚህም መሰረት ሲዳማ በህዝበ ውሳኔዉ ድምጽ ከሰጡ መራጮች ከ98% በላይ የሚሆኑት ሲዳማ ክልል እንዲሆን ድምጽ ሰጥተዋል፡፡
በ5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባኤው የደቡብ ክልል ምክር ቤት ለአዲሱ የሲዳማ ክልል ስልጣን አስረክቧል፡፡
ከደቡብ ክልል ጋር የመለያየት ሂደቶች አጠናቅቆ ሰኔ 2020 ስልጣን የተረከበው የሲዳማ ክልል ሐምሌ 4/2020 በይፋ ክልል ሆኖ ተመስርቷል፡፡