በወቅታዊው የድንበር ግጭት ላይ ውይይት እንዲደረግ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ጥያቄ ሱዳን ውድቅ አደረገች
ሱዳን “በኢትዮጵያ ይዞታ ስር የነበረውን ግዛቴን አስመልሻለሁ” ብላለች
የሱዳን እና የኢትዮጵያ ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ በድንበር ማካለል ዙሪያ ውይይት ጀምሯል
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ባለው የድንበር ማካለል ዙሪያ የከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴውን ውይይት ማስጀመራቸው ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ ከኢትዮጽያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በጽህፈት ቤታቸው ከተገናኙ በኋላ ነው የኮሚቴው ውይይት የተጀመረው፡፡
የሱዳን እና የኢትዮጵያን ግንኙነት በማይጎዳ መልኩ የድንበር ማካለሉን ጉዳይ ለማስፈጸም፣ በሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ እና የፖለቲካ መሪዎች መካከል ግልጽ ውይይት እንዲደረግም ስምምነት ተደርሷል፡፡
ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴው ፣ የድንበር ማካለሉ ስራ እንዲሳካ የሚረዱ ማዕቀፎችን የሚያዘጋጅ ሲሆን ለድንበር ማካለል ኮሚቴ ውይይት የሚሆን አጀንዳ እና የሎጂስቲክስ አቅርቦት ላይም ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከድንበር ማካለሉ ጉዳይ በተጨማሪ አሁን በድንበር ላይ ስላለው ሁኔታም ውይይት እንዲደረግ ትናንት ከኢትዮጵያ በኩል የቀረበውን ጥያቄ ሱዳን መቀበል እንዳልፈለገች የሀገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
ሱዳን አሁን ከድንበር ማካለል ጉዳይ ውጭ በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ ባለፉት ቀናት በተፈጠረው ጉዳይ ላይ መወያየት እንደማትፈልግ ገልጻለች ነው የተባለው፡፡
የሱዳን መንግስት “ላለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ የተያዘብኝን መሬት በወታደራዊ ኃይል አስመልሼ በድንበር አካባቢ ሉዓላዊነቴን አስከብርያለሁ” በማለት መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡
በትናንትናው ዕለት የሱዳን መንግሥት ቃል አቀባይ እና የማስታወቂያ ሚኒስትር ፈይሰል ሙHመድ ሳሊህ የሀገሪቱ ጦር “በኢትዮጵያ ተይዘው የነበር በርካታ ቦታዎችን መልሶ ተቆጣጥሯል” ብለዋል፡፡ ይሁንና ገና ያልተመለሱ ጥቂት ቦታዎች እንደሚቀሩም አንስተዋል፡፡ የዒትዮጵያ አርሶአደሮች ባለፉት ዓመታት ወደ ሱዳን ግዛት እየገፉ በመግባት በርካታ ስፍራዎችን ቢቆጣጠርም “የሱዳን የቀድሞው ስርዓት የኢትዮጵያን መንግስት ላለማስቀየም በሚል በዝምታ ተመልክቶ ቆይቷል” ያሉት ቃል አቀባዩ ይህ ሁኔታ አሁን እየተቀየረ ስለመሆኑ አውስተዋል፡፡ “ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በድንበር ላይ ካለው ግጭት ጋር በተያያዘ ለሚፈጠር ማንኛውም ጉዳይ ዝግጁ ናት” ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የድንበር ማካለል ስራ እስካላለቀ ድረስ ፣ የኢትዮጵያ አርሶአደሮች በኪራይም ይሁን በማንኛውም መልኩ ወደ ሱዳን ግዛት ገብተው እርሻ እንዲያከናውኑ ሀገሪቱ የመስማማት ፍላጎት እንደሌላትም ነው የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ትናንት ካርቱም ላይ ባደረጉት ንግግር ከጥቅምት 30 ጀምሮ የሱዳን ጦር በኢትዮጵያ ላይ ፣ በከባድ መሳሪያዎች እና በወታደራዊ ተሸከርካሪዎች በመታገዝ ፣ ጥቃት ሲፈጽም መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከጀመረ ከ6 ቀናት በኋላ በተፈጸመው በሱዳን ጦር ጥቃት በርካታ ንጹኃን ከመገደላቸው እና ከመቁሰላቸው በተጨማሪ የአርሶአደሮች ሰብል መዘረፉን እና ካምፖች መጎዳታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ሱዳን በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ አስመልሻለሁ ባለችው አካባቢ ከፍተኛ ጦር አስፍራለች፡፡