ጾም የመጾም ጥቅሞች ምን ምን ናቸው?
ጾም መጾም ከመንፋዊ ጥቅሞቹ በተጨማሪ በርካታ የጤና ጥቅሞች አሉት
ጾም መጾም የተጠራቀመ ስብ እና ስኳርን ከማስወገድ ጀምሮ በሰውነታችን ውስጥ ያሉ ጎጂ ንጥረ ነገሮችን ለማስወገድም ይጠቅማል ተብሏል
ጾም የመጾም ጥቅሞች ምን ምን ናቸው?
አሁን ያለንበት ወቅት የእስልምናም ሆነ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች የሚጾሙበት ወቅት ነው፡፡
ይህ የጾም ወቅት አማኞች በመጾማቸው ከሚያገኙት መንፈሳዊ ጠቀሜታ ባለፈ ግን የተለያዩ ስነ ህይወታዊ ጥቅሞችን እንደሚያገኙ በተለያዩ ጊዜያት የወጡ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡
እንደ ተመራማሪዎች ገለጻ ከሆነ ሰዎች ሲጾሙ አልያም ለረጅም ሰዓታት ከምግብ ውጪ ሲሆኑ ሰውነታችን ያጠራቀማቸውን ስብ መጠቀም የሚጀምር ሲሆን ይህም በሰውነት ውስጥ የተጠራቀመ ስብን ለማስወገድ ይረዳል፡፡ይህም ሰውነታችን የተስተካከለ ቅርጽ እንዲኖረው ይጠቅማል፡፡
እንዲሁም ሰውነታችን መግብ እንዳልተመገብን ሲረዳ በራሱ በሽታ የመከላከል አቅም ማዳበሩ ከጾም ከሚገኙ ጥቅሞች መካከል አንዱ ሲሆን ሰውነታችን ጎጂ ንጥረ ነገሮችን ለማስወገድ ይረዳዋል፡፡
በጾም ወቅት ሰውነታችን ምን ለውጥ ያስተናግዳል?
ሌላኛው የጾም ጥቅም ሰውነታችን ውስጥ የተጠራቀመ ስኳርን ለማስወገድ የሚረዳ ሲሆን በተለይም አንጀታችን ውስጥ የተጠራቀመ ምግብ አለመኖር ራሱን እንዲያጸዳ እና የተስተካከለ የምግብ ልመት እንዲኖረንም ያደርጋል ተብሏል፡፡
ጾም መጾም ከዚህ በፊት የተጠራቀመ ስብ እና ስኳርን ለማስወገድ ከመርዳቱ ባለፈ ተጨማሪ አላስፈላጊ ውፍረት እንዳይመጣብን ያግዛል፡፡
እንዲሁም ጾም መጾም ለሰውነታችን የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ህዋሳት ራሳቸውን እንዲተኩ፣ እንዲያድሱ እና እረፍት እንዲያገኙ እንደሚያደርግም እነዚሁ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ጾም መጾም የተስተካከለ የነርቭ ስርዓት እንዲኖረን፣ በሽታ የመከላከል አቅማችን እንዲጎለብት እና የማሰላሰል አቅማችን እንዲያድግም በማድረግ ይታወቃል፡፡