ማላዊ የአስተራ ዘኒካ ምርት የሆኑ 20 ሺህ ዶዝ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን አቃጠለች
ሀገሪቱ ክትባቱን ያቃጠለችው የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ስላለፈ መሆኑን ገልጻለች
ማላዊ የዓለም ጤና ድርጅት ማሳሰቢያን ወደ ጎን በማለት ነው ክትባቱን አቃጥላለች
ከ500 ሺህ በላይ ዶዝ የአስተሬ ዜኒካ ምርት የሆኑ የኮሮና ቫይረስ ከትባትን ከ2 ወር በፊት ተረክባ ነበር።
ማላዊ ከዓለም ጤና ድርጅት ከተረከበቻቸው ውስጥ 20 ሺህ ዶዝ ክትባቱ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው አልፏል በሚል በእሳት እንዲቃጠል በማድረግ ማስወገዷን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
የዓለም ጤና ድርጅት ፤የአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል እንዲሁም መድሀኒት አምራቹ አስተራ ዜኒካ ማላዊ ክትባቶቹን እንዳታቃጥል ቀድመው አሳስበው የነበረ ቢሆንም ሀገሪቱ ግን ማሳሰቢያውን ችላ ብላለች።
20 ሚሊዮን ህዝብ ብዛት ያላት ማላዊ ለዜጎቿ ደህንነት ስትል የተቋማቱን ማሳሰቢያ እንደማትተገብር የሀገሪቱ ጤና ሚኒስትር ጆሹዋ ማላንጎ ተናግረዋል።
በማላዊ አስካሁን ድረስ 34 ሺህ 216 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሲሆን ከ1 ሺህ በላይ ዜጎች ደግሞ በዚሁ ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል።
ሀገሪቱ ቫይረሱን ለመከላከልም ከ212 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎቿ ክትባቱን የሰጠች ሲሆን በቂ የክትባት መጠን በመጠባበቂያነት ማስቀመጧንም አስታውቃለች።
የዓለም ጤና ድርጅት በህንድ የኮሮና ቫይረስ መስፋፋቱን ተከትሎ ለአፍሪካዊያን የክትባት አቅርቦት እጥረት ያጋጥማል የሚል ስጋት እንዳለው ከቀናት በፊት ማሳወቁ ይታወሳል።