የማሊ ፓርላማ የአምስት አመት የዲሞክራሲያዊ ሽግግር እቅድን አጸደቀ
ውሳኔ ወታደራዊ ጁንታው የሲቪል አስተዳደርን ለመመለስ የገባውን ቃል የሚቀለብስ በመሆኑ አነጋጋሪ አድርጎታል
የጸደቀው ህግ የወደፊት ምርጫ በየትኛው ቀን ሊካሄድ እንደሚችል በግልጽ ያስቀመጠው ነገር የለም
የማሊ ህግ አውጪዎች በስልጣን ላይ ያለው ወታደራዊ ጁንታ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በትረ ስልጣን ጨብጦ እንዲቆይ የሚያስችል እቅድ አጸደቀ፡፡
የማሊ ፓርላማ ውሳኔ እንደፈረንጆቹ ነሃሴ 2022 መፍንቅለ መንግስት በማካሄድ ስልጣን የጨበጠው ወታደራዊ ኃይል የገባውን ቃል የሚቀለብስ በመሆኑ አነጋጋሪ አድርጎታል፡፡
የማሊ ወታደራዊ ጁንታ ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ የካቲት 2022 ምርጫ አካሂዳለው ቢልም ካለው የደህንነት ስጋት አንጻር ባለፈው አመት ታህሳስ ወር ላይ ከ6 ወር እስከ አምስት አመት በስልጣን ላይ ሊቆይ የሚችልበት ሃሳብ ማቅረቡ አይዘጋም፡፡
በዚህም በትናንትናው እለት 121 መቀመጫዎች ካሉት የማሊ ጊዜያዊ ፓርላማ 120 አባላት ወታደራዊ ጁንታው እስከ አምስት አመት ድረስ እንዲያስተዳድር የሚያስችል ድምጽ መስጠታቸው ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘገቧል።
የወታደራዊ ጁነታው መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ የሲቪል አገዛዝን ለመመለስ ቃል ቢገቡም የጸደቀው ህግ የወደፊት ምርጫ በየትኛው ቀን ሊካሄድ እንደሚችል በግልጽ ያስቀመጠው ነገር የለም፡፡
የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ/ ኢኮዋስ/ በማሊ ከተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ማእቀብ የጣለው ባለፈው ወር እንደነበር ይታወሳል፡፡
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ማሊ ባለፉት ሁለት ዓመታ ውስጥ ሁለት ጊዜ በአገሪቱ ወታደሮች መፈንቅለ መንግስት ተፈጽሟል።
ኢኮዋስ ማእቀቡን የጣለው ስልጣን በሀይል የተቆጣጠረው የማሊ ጁንታ ምርጫ የሚያደርግበትን ጊዜ አዲሱ የፈረንጆቹ 2022 ዓመት ከመግባቱ በፊት ምርጫ የሚያካሂድበትን እቅድ እንዲያሳውቅ ጠይቆ ምላሽ ባለማግኘቱ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም የአኮዋስ አባል ሀገራት ከማሊ ጋር የሚደረጉ የገንዘብ ዝውውሮችን ከማገድ ጀምሮ ሌሎች የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን ሊያደርጉ እንደሚችልም የኢኮዋስ አባል ሀገራት ገልጸው ነበር።
የማሊ ጁንታ ከሁለት ዓመት በፊት በምርጫ አሸንፈው የአገሪቱ ፕሬዘዳንት የነበሩት አቡበከር ኬታን በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን መቆጣጠሩ ይታወሳል።