በስህተት የምጽዋት ሳጥን ውስጥ የገባውን አይፎን ስልክ አልመልስም ያለው የሂንዱ ቤተ መቅደስ
ህንዳዊው የሂንዱ እምነት ተከታይ ገንዘብ ሲለግስ ከእጁ አምልጦ በምጽዋት ሳጥን ውስጥ የገባውን አይፎን ማስመለስ ፈተና ሆኖበታል
የሀይማኖቱ ሰዎች ሳጥኑ ውስጥ የገባው እቃ በሙሉ የቤተ መቅደሱ ንብረት ነው በሚል አቋማቸው ጸንተዋል
የሂንዱ እምነት ተከታይ የሆነው ህንዳዊ በቤተ መቅደስ ውስጥ በሚገኝ የምጽዋት ሳጥን ውስጥ ገንዘብ ሲለግስ ከእጁ አምልጦ የገባው አይፎን ስልክ እንደማይመለስለት ተነግሮታል።
ህንዳዊው አማኝ ባለፈው ወር ከቤተሰቡ ጋር “በቲሩፖሩር” የሚገኘውን “የአሩልሚጉ ካንዳስዋሚ” ቤተመቅደስን እየጎበኘ በነበረበት ወቅት ነበር በብረት የምጽዋት ሳጥን ውስጥ ስልኩ የገባው፡፡
ዲነሽ በሚል ስያሜ የሚጠራው ሰው ወደ ቤተ መቅደሱ ባለስልጣናት ጋር ቀርቦ ጉዳዩን አስረድቶ ንብረቱ እንዲመለስለት ሲጠይቅ ያገኝው ምላሽ አስገራሚ ነበር፡፡
በፈቃደኝነትም ሆነ በአጋጣሚ ወደ ሳጥን ውስጥ የገባ ማንኛውም ነገር የአምላክ ንብረት ነው ያሉት የቤተ መቅደሱ ሃላፊዎች ንብረቱን ለመመለስ ህግ አይፈቅድልንም ብለዋል፡፡
በተሰጠው ምላሽ ግራ የተጋባው ህንዳዊ ስልኩን እንዲመልሱለት በተደጋጋሚ እየተመላለሰ ቢጠይቅም የተሰጠው ምላሽ አንድ አይነት ሆኗል፡፡
ዲነሽ በጉዳዩ ተስፋ ሳይቆርጥ ለሂንዱ ሃይማኖታዊ እና በጎ አድራጎት ስጦታዎች ባለስልጣን ቅሬታውን በማሰማት ስልኩ እንዲመለስለት ጠይቋል፡፡
ሆኖም ከሂንዱ ሃይማኖታዊ እና በጎ አድራጎት ስጦታዎች ባለስልጣን ያገኘው ምላሽ መፍትሄ የሚሆን ሳይሆን ተስፋ የሚያስቆርጥ ነበር፡፡
ባለስልጣኑ ልገሳው ባለማወቅ የተደረገ ቢሆንም ማንኛውም ስጦታ ወደ ሳጥን ውስጥ ከገባ በኋላ “ዴቲ” ወደተባለው የቤተመቅደሱ አምላክ ስለሚሄድ አስተዳደሩ ንብረቱን ለምእመናን እንዲመልስ ህጎች አይፈቅዱም የሚል ተመሳሳይ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
አማኙ ስልኩ ሰላማይመለስለት ከስልኩ ውስጥ ማውጣት የሚፈልገው መረጃ ካለ የቤተ መቅደሱ ሰዎች እንዲተባበሩት ብቻ ማድረግ እንደሚችል ባለስልጣኑ ለአማኙ ነግሮታል፡፡
በህንድ የማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት የተሰራጨው አነጋጋሪው ጉዳይ ስር በርካቶች “የሰውን ንብረት ያለፈቃድ መውሰድ ከስርቆት አይተናነሰም” ሲሉ ተቃዎሟቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡