ህንጻ ተከራይቶ የራሱን ፍርድቤት የከፈተው ህንዳዊ በቁጥጥር ስር ዋለ
ሀሰተኛው ዳኛ ጓደኞቹን እንደ ጠበቃ ቀጥሮ የበርካታ ሰዎችን አቤቱታዎች ተቀብሎ ውሳኔ ሲያሳልፍ ነበር ተብሏል
ይግባኝ የጠየቀ ባለጉዳይ ግን ሀሰተኛው ፍርድቤት ከአምስት አመታት አገልግሎት በኋላ እንዲጋለጥ አድርጓል
በህንድ የራሱን ፍርድቤት ከፍቶ ሲሰራ የነበረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በጉጅራት ህንጻ ተከራይቶ “የጋንድሂንጋር ወረዳ ፍርድቤት” የከፈተው ሀሰተኛ ዳኛ ሞሪስ ክርስቲያን ይባላል።
ህጋዊ ጉዳዮችን እንዲያከናውን ምንም አይነት ፈቃድ የሌለው ክርስቲያን ጓደኞቹን ጠበቃ አድርጎ ቀጥሮ እንደነበር ኢንዲያን ታይምስ አስነብቧል።
የክርስቲያን ፍርድቤት ከ2019 ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ አቤቱታዎችን ተቀብሎ ውሳኔ ሲያሳልፍ ቆይቷል።
አብዛኞቹ የተመለከታቸው ጉዳዮች ከመንግስት መሬት ጋር የተያያዙና ከፍተኛ ጉቦ የሚገኝባቸው ናቸው የተባለ ሲሆን፥ በመቶዎች በሚቆጠሩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ማሳለፉ ተነግሯል።
ሀሰተኛው ፍርድቤት ጉዳያቸውን ከሚመለከትላቸውና በፈለጉት መንገድ ከሚወስናላቸው ሰዎች ገንዘብ ሲቀበል መቆየቱ ነው የተዘገበው።
በአህመዳባድ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ጉዳይ ያሳለፈው ውሳኔ ግን የግለሰብ ፍርድቤቱ ከአምስት አመታት በኋላ እንዲጋለጥ አድርጎታል።
ከ11 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚያወጣ መሬት ከማዛጋጃ ቤቱ ተነጥቆ ለከሳሾች እንዲተላለፍ ያሳለፈው ውሳኔ ይግባኝ ተጠይቆበት በከፍተኛ ፍርድቤት ሲታይ ነው ጥርጣሬው የጀመረው።
በተደረገው የማጣራት ስራም ፍርድቤቱ ምንም አይነት ፈቃድ በሌለው ዳኛ የተከፈተና ጠበቃ ተብለው የተቀጠሩትም የሞሪስ ክርስቲያን ጓደኞች መሆኑ ይደረስበታል።
የጉጅራት ከፍተኛ ፍርድቤት በግለሰቡ በተከፈተው ፍርድቤት የተላለፈውን ውሳኔ ሽሮ ሀሰተኛው ዳኛና ተባባሪዎቹ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አዟል።
በፈረንጆቹ 2007 በተመሳሳይ ድርጊት ለሶስት ወራት ታስሮ የነበረው ክርስቲያን አምስት አመት ሙሉ ፍርድቤት ከፍቶ ሲሰራ ሳይደረስበት መቆየቱ ግን በርካቶችን አስገርሟል።
ግለሰቡ “የአለማቀፉ ባር ካውንስል” አባል ነኝ፤ በህግ ዲግሪ አለኝ ቢልም የተባለው ምክርቤት የሌለ እና የትምህርት ማስረጃዎቹም ሀሰተኛ መሆናቸው ነው የተገለጸው።
ሀሰተኛው ዳኛ ሞሪስ ክርስቲያን “መልካም ሰዎች ወደ እስርቤት ይወረወራሉ፤ የሰዎችን ችግር በመፍታቴ ብቻ የእኔም እጣፈንታ እስርቤት ሆኗል” ብሏል።