እናት የልጇን የረሃብ አድማ ለማስቆም ስልክ ስትገዛ የሚያሳይ ቪዲዮ ከተለቀቀ በኋላ በታዳጊው ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ እየደረሰበት ነው
በህንድ አዲስ ስማርት ስልክ ካልተገዛልኝ ምግብ አልቀምስም ያለው ታዳጊ መነጋገሪያ ሆኗል።
ታዳጊው የእናቱን ልብ ለማራራት ለሶስት ቀናት የረሃብ አድማ ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን፥ ህንዳዊ ጋዜጠኛ ለታዳጊው አይፎን ስልክ ሲገዛለት የሚያሳይ ቪዲዮ አጋርቶም ሚሊየኖች ተመልክተውታል።
“አበባ በመሸጥ ነው ህይወቴን የምመራው፤ ላለፉት ሶስት ቀናት ምግብ ስላልተመገበ ስልኩን እንዲገዛ ብር ሰጥቸዋለሁ” ሲሉ ይደመጣሉ የታዳጊው እናት።
ጥሪታችን ሁሉ ለልጃቸው ስልክ መግዣ ማዋላቸው ያሳሰባቸው እናት፥ “ደስተኛ ነኝ ነገር ግን ሰርቶ ገንዘቡን ሊመልስኝ ይገባል” ማለታቸውንም ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።
ታዳጊው ከእናቱ ያገኘውን ብር ይዞ ስልኩን ሲገዛ የሚያሳየው ቪዲዮ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አስተያየት ሰጥተዋል።
አብዛኞቹ አበባ ሸጣ የምትመግበውን እናቱን እንዴት እንዲህ ይጨክንባቸዋል፤ እናት ልጇን ላለማጣት ምንም ነገር እንደምታደርግ በማሰብ የረሃብ አድማ መጀመርስ ምን አይነት እብደት ነው የሚሉና የታዳጊውን ሀሳበ ቢስነት የሚያጣጥሉ ናቸው።
ታዳጊው ምንም ስራ ሳይኖረው ቅንጡ ስልክ ከደሃ እናቱ ሲያስገዛ ደስታው ይነበባል፤ የእናቱ ስሜት ግን ይበልጥ ይናገራል።
የታዳጊው ድርጊት ወጣቱ ትውልድ ስማርት ስልኮችን እንደ ደረጃ እና እድገት ማሳያ የማድረግ አባዜ አመላካች ነው ያሉ አስተያየት ሰጪዎችም ህንዳዊው ታዳጊ ቢያንስ በስልኩ ስራ ሰርቶበት ለእናቱ ያወጡትን ወጪ እንዲመልስላቸው ጠይቀዋል።
የስማርት ስልኮችን ለመግዛትና ለማስገዛት ሰዎች አስገራሚ ውሳኔዎችን ሲወስኑ ይታያል።
ከአምስት አመት በፊትም ቻይናዊው ወጣት አይፎን ስልክ ለመግዛት አንድ ኩላሊቱን መሸጡ መዘገቡ ይታወሳል።