ለ18 አመታት ያገለገላቸውን ተሸከርካሪ ልክ እንደ ሰው በክብር ያስቀበሩት ህንዳውያን መነጋገርያ ሆኑ
4500 ዶላር ፈጅቷል በተባለው የቀብር ስነስርአት ላይ ከ1500 በላይ ታዳምያን ተሳትፈዋል
የመኪናው ባለቤት ህንዳውያን ቤተሰቦች ለሚገኙበት የሀብት ደረጃ መኪናው ባለውለታችን ነው ብለዋል
አንድ የህንድ ቤተሰብ 1500 የሚጠጉ ሰዎች በተገኙበት ታላቅ የቀብር ስነስርአት ለ18 አመት ያገለገላቸውን “ሱዙኪ ዋገን” መኪና ወደ መቃብር መሸኘታቸው መነጋገርያ ሆነዋል፡፡
በተለምዶ ከቁሳዊ ነገሮች ጋር መጣባቅ አያስፈልግም ይባላል፤ ይህ አባባል ግን 4500 ዶላር ለመኪና ቀብር ስነስርአት ወጪ ላደረጉት ህንዳዊያን ቤተሰቦች አይሰራም፡፡
በጉጅራት ፓዳርሺንጋ መንደር የፖላራ ቤተሰብ አባላት “ሱዙኪ ዋገን አር” የተሰኝ ቆየት ያለ መኪና ልክ እንደ ሰው ልጅ በክብር በቀብር ተሰናብተውታል።
ህንዳዊያኑ "እድለኛ" መኪና ብለው የሚጠሩትን ተሸከርካሪ አሁን ለሚገኙበት የሀብት ደረጃ መነሻ ነው ብለው ያምናሉ፡፡
ለሁለት አስርት ዓመታት ከሚጠጋ የታማኝነት አገልግሎት በኋላ በቆሻሻ ቦታ ላይ ከመጣል ይልቅም በትክክለኛው መንገድ ሊሰናበቱት በመፈለጋቸው ቀብሩን እንዳስፈጸሙ ይናገራሉ፡፡
ፓትራርክ ሳንጃይ ፖላራ የተባለው የቤተሰቡ አባል “አውዲ” የተሰኝውን ቅንጡ መኪና ጨምሮ ሌሎች ብዙ ውድ መኪኖች እንዳሉት ይናገራል። ነገር ግን አሮጌው ሱዙኪ ለቤተሰቡ ብልጽግናን ለማስገኘት በነበረው አስተዋፅዖ ልክ እንደቤተሰባችን አባል ነው ብሏል፡፡
15 ጫማ ጥልቀት ያለው የመቃብር ጉድጓድ ውስጥ ቀብሩ ሲፈጸም በሀዘን ሙዚቃዎች ታጅቦ መኪናው በቀለማት ባሸበረቁ የአበባ ጉንጉኖችም አጊጦ ነበር።
ሀይማኖታዊ ስነስርአቱን ጨምሮ ለመኪናው ሀውልት የተሰራለት ሲሆን አጠቃላይ የቀብር ስነስርአቱ 4500 ዶላር ወጪ እንደተደረገበት ተሰምቷል፡፡
ሰዎች ለአግልግሎቱ ካላቸው አድናቆት የተነሳ መኪናቸውን በክብር ሲያስቀብሩ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ አይደለም። ዩራጓዊው አርሶ አደር አልሲዲስ ራቨል እ.ኤ.አ በ2017 ከ48 አመታት በላይ አገልግሎት በኋላ “ፎርድ ኤፍ -350” የተባለ መኪናቸውን በተመሳሳይ በክብር አስቀብረዋል፡፡