ይህ ሰው መሬት ውስጥ በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ ይኖራል የተባለ ሲሆን ከ16 ዓመቱ ጀምሮ ራሱን ከሴቶች ማራቁ ተገልጿል
ሴቶችን በመፍራት ራሱን ደብቆ የሚኖረው የ71 ዓመቱ ድንግል ሰው
ሩዋንዳዊው ካሊአ ንዛምዊታ አሁን ላይ የ71 ዓመት አዛውንት ሲሆን ሴቶችን የመቅረብ የተጋነነ ፍርሃት እንዳለበት ተገልጿል፡፡
ይህ ግለሰብ ከ16 ዓመቱ ጀመሮ ለተቃራኒ ጾታ የተጋነነ ፍርሃት አለበት የተባለ ሲሆን በዚህ ፍርሃቱ ምክንያትም ራሱን መሬት ውስጥ ደብቆ እንዲኖር አድርጎታል ተብሏል፡፡
ከሴቶች ጋር ላለማውራት ፊት ለፊት ላለመገናኘት ሲል ራሱን ደብቆ ሲኖር 55 ዓመት እንደሞላው በአፍሪካ ያሉ ለየት ያሉ ክስተቶችን የሚዘግበው አፍሪማማክስ ቲቪ ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ ይህ የ71 ዓመት አዛውንት ድንግል ሲሆን ራሱን ከሴቶች ደብቆ መኖር ከጀመረ 55 ዓመት ሆኖታል፡፡
ይሁንና ከሴቶች ራሴን ደብቄያለሁ የሚለው ይህ አዛውንት ህይወቱን የሚኖረው ሴቶችን ጨምሮ የአካባቢው ማህበረሰብ በሚሰጡት ምግብ እና አልባሳት ነው ተብሏል፡፡
ግለሰቡ እስካሁን ህመም አጋጥሞት ወደ ህክምና ተቋማት ሄዶ አያውቅም የተባለ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪ ሴቶች በሚኖርበት ጉድጓድ አቅራቢያ ምግቡን አልያም ሌሎች እርዳታዎችን ካስቀመጡለት በኋላ መሄዳቸውን አረጋግጦ እንደሚወስድ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ሴት ተናግረዋል፡፡
ይህች ሴት አክላም እኛ ቀርበን እንድናወራው እና እንድናየው ፈጽሞ አይፈልግም ነገር ግን ከርቀት ሆነን በምናስቀምጥው ምግብ እና ልብስ ግን ህይወቱን እየመራ ነው ስትልም ተናግራለች፡፡
እንደ ህክምና ባለሙያዎች አስተያየት ግለሰቡ ጋይኖፎቢያ ወይም በተጋነነ መልኩ የተቃራኒ ጾታን መፍራት ህመም ተጠቂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡