ከ12 አመት በፊት የጠፋን 600 ሚሊየን ፓውንድ ፍለጋ፤ በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ስፍራ
ሚስቴ የቢትኮይን ዋሌት የያዘ ሃርድ ድራይቭ የያዘ ቦርሳ ቆሻሻ መስሏት ጥላብኛለች የሚለው እንግሊዛዊ ሃብቱን ዳግም ለማግኘት ቆሻሻ የሚደፋበትን ስፍራ ለመግዛት ጠይቋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/11/273-181706-skynews-james-howells-bitcoij-6825007_700x400.jpg)
ግለሰቡ ፍለጋውን ለማካሄድ በኒውፖርት ከተማ ምክርቤት ላይ ያቀረበው ክስ ውድቅ ተደርጎበታል
የኮምፒውተር ባለሙያው ጀምስ ሆውልስ ከፈረንጆቹ 2023 ጀምሮ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን ሲያሳልፍ ቆይቷል።
በአንድ ቀን 600 ሚሊየን ፓውንድ ዋጋ ያለው ቢትኮይን ያጣው ሆውልስ ከአስር አመት በላይ የጠፋበትን ሃብት ዳግም ለማግኘት ሲማስን ቆይቷል።
የ39 አመቱ ሆውልስ ሚሊየነር የሚያደርገው ቢትኮይን ከቆሻሻ ጋር ተጥሏል ብሎ ካመነ ጀምሮ ያልጠየቀው የኒውፖርት ከተማ አመራር የለም፤ እስከ ከፍተኛ ፍርድቤት ድረስም አምርቷል።
ግለሰቡ ሚስቱ የቢትኮይን ዋሌት የያዘ ሃርድ ድራይቭ የያዘ ጥቁር ቦርሳ ቆሻሻ መስሏት እንደጣለችው ካረጋገጠ በኋላ ቆሻሻ የሚከማችበትን ስፍራ በየእለቱ ይጎበኘዋል።
በደቡብ ዌልስ የምትገኘው የኒውፖርት ከተማ ምክርቤትም ሚስቱ ሃርድ ድራይቩን የጣለችበትን የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ስፍራ እንዲያስስ ፈቃድ እንዲሰጠው አልያም የ495 ሚሊየን ፓውንድ ካሳ እንዲከፍለው በከፍተኛ ፍርድቤት ከሶ ሲከራከር ቆይቷል።
የከተማዋ ምክርቤት የሀውልስ ሃርድ ድራይቭ ከቆሻሻ ማጠራቀሚያ ስፍራው ውስጥ ከገባ በኋላ ንብረትነቱ የከተማው እንጂ የእርሱ አይደለም ሲል ተከራክሯል።
ፍርድቤቱም ባለፈው ወር የምክር ቤቱ ምላሽ አሳማኝ ነው በሚል 600 ሚሊየን ፓውንድ የሚያወጣ ቢትኮይን ጠፍቶብኛል ያለው ግለሰብ በቆሻሻ ማጠራቀሚያው የጠፋውን ሃርድ ድራይቭ መፈለግ አይችልም ብሎ ወስኗል።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የአመታት ተስፋውን ይጨለመበት ሆውልስ በትናንትናው እለት ሌላ መርዶ ሰምቷል፤ የቆሻሻ ማጠራቀሚያው በ2025 አልያም በ2026 ሊዘጋ ነው የሚል።
"የቆሻሻ ማጠራቀሚያው 80 ወይም 90 በመቶው ሞልቷል፤ ነገር ግን በዚህ ፍጥነት እንዲዘጋ ይወሰናል ብዬ በፍጹም አልጠበቅኩም" ያለው ወጣት፥ የኒውፖርት ከተማ አስተዳደር የቆሻሻ ማጠራቀሚያውን እንድገዛውና ፍለጋየን እንዳካሂድ ይፍቀድልኝ ሲል ጥሪውን አቅርቧል።
የቆሻሻ መድፊያው ለሌላ ኢንቨስትመንት ከተፈለገም ከአልሚዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ ነኝ ማለቱን ዘጋርዲያን አስነብቧል።
የኒውፖርት ከተማ ከሆውልስ ለቀረበው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም ተብሏል።
ከ12 አመት በፊት የጠፋውን ሃርድ ድራይቭ ለመፈለግ ለአመታት የተከመረ ቆሻሻን ማንቀሳቀስ ይፈልጋል፤ ይህም በርካታ የሰው ሃይል እና ገንዘብ ይጠይቃል። ጀምስ ሆውልስ ግን የተከፈለውን መስዋዕትነት ከፍሎ አዕምሮውን እረፍት ለነሳው ጉዳይ ምላሽ መስጠት ፈልጓል።