ሩሲያ የተጣለባትን ማዕቀብ ለማምለጥ ቢትኮይንን እየተጠቀመች ነው ተባለ
ከቻይና እና ቱርክ ጋር የሰመረ ንግድ ያላት ሩሲያ በቢትኮይን ግብይት እየፈጸመች እንደሆነ ተገልጿል
ሩሲያ በቅርቡ የቢትኮይን ግብይት እንዲደረግ የሚፈቅድ ህግ አጽድቃለች
ሩሲያ የተጣለባትን ማዕቀብ ለማምለጥ ቢትኮይንን እየተጠቀመች ነው ተባለ።
ሩሲያ ጦሯን ወደ ዩክሬን ግዛቶች መላኳን ተከትሎ ምዕራባዊያን ሀገራት በሞስኮ ላይ ከ12 ሺህ በላይ ማዕቀቦችን ጥለዋል።
ይህን ተከትሎ ሩሲያ ከዚህ በፊት የነበሯትን የንግድ ልውውጦች እንደልብ ማድረግ አልቻለችም ተብሏል።
ይህን ለማምለጥም እንደ ቢትኮይን ያሉ የምናባዊ መገበያያ መንገዶችን እየተጠቀመች እንደሆነ የሩሲያ ፋይናንስ ሚንስትር ተናግረዋል ።
ሚንስትሩ አንቶን ሲሉአኖቭ ለሩሲያ 24 በሰጡት ቃለ መጠይቅ ሩሲያ ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር የቢትኮይን ግብይት እንዲያደርጉ ፈቅዳለች ብለዋል።
ሩሲያ በተለይም ዋነኛ የንግድ አጋር ከሆኑት ቻይና እና ቱርክ ጋር የቢትኮይን ግብይት እያደረጉ እንደሆነም ሚንስትሩ ጠቅሰዋል።
የቢትኮይን ልማት እየተካሄደባቸው ካሉ የዓለማችን ሀገራት መካከል ሩሲያ ቀዳሚዋ ስትሆን ይህ ግብይት ማዕቀቦችን መቋቋም እንድትችል አስችሏታል ተብሏል።
ሚንስትሩ አክለውም አሜሪካ በዶላሯ ተጽዕኖ ምክንያት ሀገራት እየቀጣች ነው ያሉ ሲሆን እንደ ቢትኮይን አይነት ግብይቶች የዶላርን አቅም ያዳክመዋል ማለታቸው ተገልጿል።
ቢትኮይን በማንኛውም ሀገር ቁጥጥር ስር አለመሆኑ ጥሩ ነው የሚሉት ሚንስትሩ በቀጣይ ዓመትም ሩሲያ የቢትኮይን እና መሰል ክሪፕቶከረንሲ ግብይቶችን ትቀጥላለችም ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከአንድ ወር በፊት የሩሲያ የንግድ ተቋማት የክሪፕቶከረንሲ ግብይቶችን እንዲያደርጉ የሚፈቅድ ህግ ላይ መፈረማቸው ይታወሳል።