በካናዳ አንድ ወጣት በጥላቻ በመነሳሳት የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ 4 ሙስሊሞችን ገደለ
ወጣቱ ግድያውን የፈጸመው በፒካፕ የጭነት መኪና በመግጨት ነው
ከአምስት የቤተሰብ አባላት አራቱን የገደለው ናታንኤል ቬልትማን አምስት ክሶች ቀርበውበታል
አንድ የ20 ዓመት ወጣት ፣ አራት የካናዳ ሙስሊም ቤተሰብ አባላትን በፒካፕ መኪና አሳድዶ መግደሉን ፖሊስ ገለፀ፡፡ ግለሰቡ ግድያውን የፈጸመው ሙስሊም በመሆናቸው በጥላቻ ተነሳስቶ ሊሆን እንደሚችል ፖሊስ በትናንትናው እለት አስታውቋል፡፡
ግድያው የተፈጸመው በካናዳ ኦንታሪዮ ግዛት ሎንዶን ከተማ ሲሆን ፖሊስ ምስክሮችን በመጥቀስ እንደገለጸው የ 20 ዓመቱ ናታንኤል ቬልትማን እሁድ ዕለት መኪናውን በፍጥነት እያሽከረከረ የመንገዱን ዳርቻ በመዝለል ዕድሜያቸው ከ 9 እስከ 74 የሆኑ አምስት የቤተሰቡ አባላትን ገጭቷል፡፡ በዚህም የ74 ፣ የ 44 እና የ15 ዓመት ሴቶች እንዲሁም የ46 ዓመት ወንድ ህይወታቸው ሲያልፍ ፣ የቤተሰቡ አባል የሆነ የ9 ዓመት ህጻን ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ሆስፒታል ይገኛል፡፡
ግድያውን የፈጸመው ወጣት በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን በአንደኛ ደረጃ ግድያ አራት ክሶች እንዲሁም በመግደል ሙከራ አንድ ክስ ቀርቦበታል፡፡ ሰኞ ዕለት በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰቡ ሐሙስ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ተገልጿል፡፡
የሎንዶን ፖሊስ መምሪያ ባልደረባ መርማሪ ፖሊስ ፓውል ዌይት “ይህአስቀድሞ የታቀደና በጥላቻ በመነሳሳት የተፈጸመ ለመሆኑ ማስረጃ አለ” ብለዋል፡፡
ተጎጂዎቹ በእስልምና እምነታቸው የተነሳ ዒላማ የተደረጉ ናቸው ብለን እናምናለን ሲሉም ዌይት ተናግረዋል፡፡
የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ በትዊተር ገፃቸው “ዜናው በጣም አስደንጋጭ ነው” ሲሉ ገልፀው “የኢስላም ጥላቻ በየትኛውም የሀገራችን ማህበረሰብ ውስጥ ቦታ የላቸውም ፡፡ ይህ ጥላቻ መሰሪ እና የሚናቅ ነው - እናም መቆም አለበት” ብለዋል፡፡ “በትናንቱ ከጥላቻ የመነጨ ጥቃት የተሸበራችሁ ሁሉ አብረናችሁ ነን ከጥቃቱ ተርፎ ሆስፒታል ካለው ህጻንም ጋር አብረን ነን” ሲሉም ገልጸዋል፡፡