የካናዳው መካነ እንሰሳት በቀርቀሀ እጥረት ምክንያት ሁለት ፓንዳዎችን ወደ መጡበት ቻይና ሊመልስ ነው
የካናዳው መካነ እንሰሳት በቀርቀሀ እጥረት ምክንያት ሁለት ፓንዳዎችን ወደ መጡበት ቻይና ሊመልስ ነው
በካናዳ የሚገኘው የካልጋሪ የዱር እንስሳት መንከባከቢያ ማዕከል (መካነ እንሰሳ) በቀርከሃ እጥረት ምክንያት ሁለት ግዙፍ ፓንዳዎችን (ድብ መሳይ እንስሳት) ወደ መጡበት ቻይና ሊመልስ መሆኑን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
የዱር እንስሳቱ የሚጠበቁበት ይህ ቦታ በሰጠው መግለጫ እንዳመለከተው ለፓንዳዎቹ ምግብ የሚሆን ቀርቀሃ የሚያስመጣው ከቻይና ነበር፡፡
ይሁንና አሁን ላይ ባለው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በረራዎች በመስተጓጎላቸው ለእንስሳቱ ምግብ የሚሆን ቀርቀሃን ወደ ካናዳ ማስገባት አልተቻለም፡፡
ሹን እና ዳ ማኦ የተባሉት መንትያ ፓንዳዎች በካናዳ እስከ ፈረንጆቹ 2023 እንዲቆዩ ስምምነት የተደረሰ ቢሆን አሁን ላይ ለምግባቸው የሚሆነው ቁሳቁስ መግባት ባለመቻሉ ወደመጡበት ቻይና እንዲመለሱ ሊደረግ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
በካናዳ ካልጋሪ የዱር እንስሳት መንከባከቢያ ቦታ ያሉት ፓንዳዎች የሚበሉት ቀርቀሃ ከቻይና በቀጥታ የሚገባ ነበር፡፡ አሁን ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚል በረራዎቹ የተሰረዙ ሲሆን የፓንዳዎቹም ህይወት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ በመሰጋቱ ይመለሳሉ ተብሏል፡፡
እንሸሳቱ የሚመገቡትን ቀርቀሃ የሚያቀርብ አዲስ አቅራቢ ለማግኘት ጥረት ቢደረግም የሎጀስቲክ ጉዳዮች እንቅፋት ሆነዋል ተብሏል፡፡የካልጋሪያ ዱር እንስሳት መንከባከቢያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክሌመንት ላንዚር አሁን ላይ ፓንዳዎቹ ምግባቸውን በቅርበት ወደሚያገኙበት ቦታ መሄድ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ፓንዳዎቹ የሚመገቡትን ቀርቀሃ በቅርበት ማግኘት አለባቸው ያሉት ኃላፊው ውሳኔው ከባድ ቢሆንም ለምንወዳቸው ፓንዳዎች ደህንነት ስንል ግን ይህንን ውሳኔ ወስነናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሹን እና ዳ ማኦ የተሰኙት ፓንዳዎች ወደ ካናዳ የመጡት በአውሮፓውያኑ 2014 ሲሆን በመጀመሪያ በቶሮንቶ የእንስሳት መንከባከቢያ ቦታ ነበር የቆዩት፡፡ አሁን ወዳሉበት ካልጋሪ የመጡት በ2018 ነበር፡፡
እነዚህን ፓንዳዎች ወደ ቻይና የመመለሱ ሁኔታ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ እንደሚሳካ ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ቻይና እነዚህን ፓንዳዎች ለወዳጅነትና ለትብብር ምልክት እንዲሆናት በማሰብ ወደ ሌሎች ሀገራት የመላክ ልምድ አላት፡፡