9 ጊዜ ተመርምራ 8 ጊዜ ኮሮና የተገኘባት ካናዳዊት ነርስ
በሁኔታው እጅግ መስጋቷን ያስታወቀችው ግለሰቧ ሌላ ተያያዥ የጤና ችግር እንዳይሆን በሚል ፈርታለች
ለ10ኛ ምርመራ ተዘጋጅታለች
9 ጊዜ ተመርምራ 8 ጊዜ ኮሮና የተገኘባት ካናዳዊት ለ10ኛ ምርመራ ተዘጋጅታለች
ካናዳዊቷ ትሬሲ ስኮፊልድ ምልክቶችን ማሳየቷን ተከትሎ ባደረገቻቸው 9 ምርመራዎች በ8ቱ በቫይረሱ መያዟ መረጋገጡን የሃገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
በወርሃ መጋቢት መገባደጃ ላይ የመጀመሪያውን ምርመራ ያደረገችው የካምብሪጅ ኦንታሪዮ ነዋሪዋ ስኮፊልድ በቫይረሱ መያዟን በምርመራው አረጋግጣ ነበረ፡፡ ከዚያ ወዲህም ‘ነጻ’ የተባለችበትን አንድ ምርመራ ጨምሮ 8 ያህል ምርመራዎችን አድርጋለች፡፡
በቫይረሱ መያዟ ከተረጋገጠበት ከመጀመሪያው ምርመራ በኋላ ለሁለት ሳምንታት ራሷን አግልላ ብትቆይም የሰውነቷ ሙቀት ከወትሮ በተለየ መልኩ ጨምሮ ከ40 ዲግሪ ሴልሺዬስ ከፍ በማለቱ እና ሌሎቹም ምልክቶች በመባባሳቸው እንደገና ተመርምራ አሁንም ቫይረሱ እንዳለባት ታረጋግጣለች፡፡ በ7 ተመሳሳይ ምርመራዎችም ይኸው ሆኗል፡፡
8ኛው ግን ከሌሎቹ በተለየ መልኩ ‘ነጻ’ ነበረ፡፡ ነገር ግን እንዲህ አይነቱ የ‘ነጻ’ ውጤት በ24 ሰዓታት ውስጥ በሚደረግ ተጨማሪ ምርመራ መረጋገጥ እንዳለበት የዓለም ጤና ድርጅት መመሪያ የሚያዝ በመሆኑ ለ9ኛ ጊዜ ባሳለፍነው እሁድ ምርመራን ታደርጋለች፡፡ ውጤቱም ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ እ.ኤ.አ መጋቢት 19/2020 ይደርሳታል በስሟ ባለው ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ እንዳስቀመጠቸው ከሆነ፡፡ ሆኖም የደስታ ሲቃ ሲተናነቃት ለነበረችው ሴት ውጤቱ እንደተጠበቀው አልሆነም፡፡ ቫይረሱ አሁንም በሰውነቷ እንዳለ የምርመራው ውጤት ያመለክታል፡፡
አሁንም ከህመሙ ያልተላቀቀችው እና 9 ጊዜ ተመርምራ 8 ጊዜ ቫይረሱ የተገኘባት ስኮፊልድ ለ10ኛ ምርመራ መዘጋጀቷን ፎክስ ኒውስ ካናዳ ቲቪ ኒውስን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
10ኛው ምርመራ ሊደረግ የሚችለው የ9ኛው ውጤት ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት 5 ቀናት ውስጥ ሊሆን እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በሁኔታው እጅግ መስጋቷን ባሰፈረችበት ጽሁፍ ላይ የደም መርጋት አለበለያዚያም ሌላ ተያያዥ የጤና ችግር እንዳይሆን የሚል ፍራቻ እንዳደረባትም ገልጻለች፡፡
የጤና ባለሙያዎች እንዲህ ዓይነት ነገር ሊያጋጥም የሚችልበት ነገር እንዳለ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ የመመርመሪያ መሳሪያዎች አያያዝና የጥራት ደረጃ ለምርመራው ትክክል መሆንና ውጤታማነት ወሳኝ ነውም ይባላል፡፡
እንዲያውም የመመርመሪያ መሳሪያዎች (ቴስት ኪትስ) ቫይረሱን በወጉ የመመርመር አቅማቸው እስከ 70 በመቶ ነው በሚል የሚናገሩ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ ይህም እንደ ኪቶቹ የጥራት ደረጃ ቢለያይም ከምርመራ ውጤቶች ሶስት እጅ ያህሉ ‘ነጻ’ ሊባሉ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው፡፡
በሙያዋ ነርስ ስትሆን ያለፉትን 2 ገደማ ወራት ራሱን በቤት ውስጥ ለይቶ ካቆየው የ17 ዓመት ልጇ ጋር ነው የምትኖረው፡፡
የሎተሪ አሸናፊም ነች፡፡ ‘ቲም ሆርቶን’ የተሰኘው የካናዳ የቡና ኩባንያ ከ7 ዓመታት በፊት አዘጋጅቶት በነበረው የሎተሪ እጣ እድል አሸናፊም ሆና ቶዮታ ኮሮላ መኪና ስለመሸለሟ በወቅቱ ወጥተው የነበሩ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡