የቀያይ ሰይጣኖቹን የዩሮፓ ሊግ ተሳትፎ የሚወስነው የኤፍኤ ዋንጫ ፍልሚያ
የከተማ ክለቦቹን ለፍጻሜ ያገናኘው ጨዋታ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግን ይታደጋል ወይስ ስንብታቸውን አይቀሬ ያደርጋል?
ዩናይትድ ከሲቲ ጋር ካደረጋቸው ያለፉት ሰባት የኤፍኤ ካፕ ጨዋታዎች በአምስቱ ማሸነፍ ችሏል
የ2023/24 የኤፍኤ ካፕ የዋንጫ ፍልሚያ ዛሬ 11 ስአት ላይ በዌምብሌይ ይካሄዳል።
የባለፈው አመት የዋንጫ ተፋላሚዎቹን ማንቸስተር ሲቲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ የሚያገናኘው ጨዋታ ለቀያይ ሰይጣኖቹ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል።
በፕሪሚየር ሊጉ ስምንተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ዩናይትድ በቀጣይ አመት በአውሮፓ መድረክ (ዩሮፓ ሊግ) ለመሳተፍ የዛሬውን የዌንብሌይ የፍጻሜ ጨዋታ ማሸነፍ ይኖርበታል።
ባለፈው አመት 2 ለ 1 ተሸንፎ በሲቲ ዋንጫውን የተነጠቀው የኤሪክ ቴን ሀግ ቡድን ዛሬም ሽንፈት ከገጠመው ከ1881/82 በአውሮፓ መድረክ ለሁለተኛ ጊዜ የማይሳተፍ ይሆናል።
በኦልትራፎርድ 3 ለ 0 በኢትሃድ ደግሞ 3 ለ 1 ያሸነፈው የፔፕ ጋርዲዮላው ሲቲ እንደባለፈው አመት የሶስትዮሽ ዋንጫ ማሳካት ባይችልም የኤፍኤ ዋንጫውን እንደሚወስድ ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ከከተማ ተቀናቃኙ ጋር ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች (በሁሉም ውድድሮች) በስድስቱ ተሸንፎ በአንዱ አቻ ወጥቷል።
በኤፍኤ ካፕ ጨዋታዎች ግን ዩናይትድ የተሻለ ውጤት አስመዝግቧል፤ ከሲቲ ጋር ካደረጋቸው ያለፉት ሰባት የኤፍኤ ካፕ ጨዋታዎች በአምስቱ ማሸነፍ ችሏል።
ዘ ሲቲዝንስ ዛሬ የሚሳካላቸው ከሆነ የፕሪሚየር ሊግ እና ኤፍኤ ካፕ ዋንጫን ለሶስት ተከታታይ አመት በማንሳት የማንቸስተር ዩናይትድ እና አርሰናልን ክብር ይጋራሉ።
የዌንብሌዩ የዛሬ የፍጻሜ ጨዋታ የማንቸስተር ዩናይትዱን አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ እጣ ፈንታ ይወስናል ተብሏል።
አሰልጣኙም ሆነ ክለቡ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት ከመስጠት ቢቆጠቡም ከዩናይትድ የ27 ነጥብ 7 በመቶ ድርሻ የገዙት ሰር ጂም ራትክሊፍ የዩናይትድን ከአውሮፓ መድረክ ገሸሽ ማለት በዝምታ ያልፉታል ተብሎ አይጠበቅም።
ከፔፕ ጋርዲዮላ ጋር ለሁለተኛ ተከታታይ አመት በኤፍኤ ካፕ ፍጻሜ የሚገናኙት ቴህ ሀግ በበኩላቸው ሙሉ ትኩረታቸው ዋንጫውን ወደ ኦልትራፎርድ ማምጣት ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።
ከቼልሲ በስምምነት የተሰናበቱት ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ፣ ቶማስ ቱኸል፣ ጋሬዝ ሳውዝጌት እና የብሬንትፎርዱ ቶማስ ፍራንክ ሆላንዳዊውን ኤሪክ ቴን ሀግ ሊተኩ ከሚችሉት አሰልጣኞች መካከል ተጠቅሰዋል።
የኤሪክ ቴን ሀግ ተፋላሚ ስፔናዊው ፔፕ ጋርዲዮላ የኤፋኤ ዋንጫውን ከፕሪሚየር ሊጉ ጋር ለሶስተኛ ተከታታይ አመት ለማንሳት ዌንብሌይ ይገኛሉ።