ባየርሙኒክ ቴን ሃግን የቱኸል ተተኪ ለማድረግ ማሰቡ ተነገረ
ሆላንዳዊው አሰልጣኝ በማንቸስተር ዩናይትድ እያስመዘገቡት ያለው ውጤት ከክለቡ እንዲለቁ ጫናውን አበርትቶባቸዋል
ቀያዮቹ ሰይጣኖች በክሪስታል ፓላስ 4 ለ 0 የተሸነፉበት ጨዋታ የቴን ሀግ የኦልትራፎርድ ቆይታ እያከተመ መሆኑን ያሳያል ተብሏል
የጀርመኑ ባየርሙኒክ የማንቸስተር ዩናይትዱን አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ የቶማስ ቱኸል ተተኪ ለማድረግ ማቀዱ ተነገረ።
የቡንደስሊጋው ክለብ ከሆላንዳዊው አሰልጣኝ ወኪል ኪስ ቮስ ጋር መነጋገሩን ስካይ ኒውስ ዘግቧል።
ባየርሙኒክ ከቴን ሀግ ጋር እስካሁን በቀጥታ ይፋዊ ንግግር አልጀመረም ቢባልም የባቫሪያኑ ክለብ አይኑን እንደጣለባቸው አውቀዋል ይላል ዘገባው።
የ54 አመቱ አሰልጣኝ ግን ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር የኤፍኤ ዋንጫን በማንሳት የዩሮፓ ሊግ ተሳትፎ ማረጋገጥ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ሲገልጹ ቆይተዋል።
ቴን ሀግ በዩናይትድ ስኬት ቢርቃቸውም በአያክስ የነበራቸው ቆይታ ለባየርሙኒክ አሰልጣኝነት እንዳሳጨቸው ነው የተገለጸው።
የባየር ሙኒክን ተጠባባቂ ቡድን ለሁለት አመት ማሰልጠናቸውም ሌላኛው ምክንያት ነው።
ቴን ሀግ ወደ አሊያንስ አሬና ካቀኑ የወቅቱ የባየር ሙኒክ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኸል ቀጣይ መዳረሻቸው ኦልትራፎርድ ሊሆን እንደሚችል ዘገባዎች እየወጡ ነው።
ቱኸል የሊቨርፑል፣ ባርሴሎና እና ጀርመን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የመሆን እድላቸው መክሰሙ ከቴን ሀግ ጋር ክለብ እንዲቀያየሩ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ተጠቁሟል።
የቴን ሀግ የኦልትራፎርድ የቁልቁለት ጉዞ
ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት ምሽት በክሪስታል ፓላስ 4 ለ 0 ተሸንፎ በፕሪሚየር ሊጉ በ54 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ዩናይትድ በዚህ የውድድር አመት 13ኛ ሽንፈቱን አስመዝግቧል፤ ይህም ከ1989/90 የውድድር አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ቀያዮቹ ሰይጣኖች በፕሪሚየር ሊጉ ከሰባተኛ በታች ደረጃን ይዘው አጠናቀው አያውቁም፤ በአሁኑ ወቅት ሶስት ጨዋታ እየቀራቸው ስምንተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ዩናይትድ ከሜዳው ውጭ ሶስት ጊዜ በአራት እና ከዚያ በላይ የጎል ልዩነት በመሸነፍ በኖቲንግሃም ፎረስት (አምስት) ብቻ ነው የሚቀደመው።
የኤሪክ ቴን ሀግ ቡድን በዚህ አመት በሁሉም ውድድሮች 81 ጎሎች ተቆጥረውበታል፤ ይህም ከ1976/77 የውድድር አመት በኋላ ከፍተኛው ነው።
ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ እስከ 35ኛው ሳምንት ድረስ የገባበት ጎል ካስቆጠረው በሶስት ይበልጣል (የጎል ልዩነቱ ነጌቲቭ ሶስት ነው)፤ ይህ አሃዝም ከ34 አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበ ነው።
ማንቸስተር ዩናይትድ በቀጣይ የዩሮፓ ሊግ ተሳትፎውን ለማረጋገጥ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር የሚያደርገውን የኤፍኤ ካፕ ፍጻሜ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።
እነዚህና ሌሎች ጉዳዮች የክለቡ ደጋፊዎች ቴን ሀግ እንዲሰናበቱ ጫና እንዲያደርጉ አስገድደዋል።