ምዕራባውያን የሩሲያ አጋር ናት ብለው የሚከሷት ቻይና በዩክሬን ሰላም እንዲመጣ ፍላጎቷ መሆኑን ገለጸች
የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ቤጂንግ ለሞስኮ ወታደራዊ እርዳታ ታቀርባለች ብሎ እንደሚያምን ገልጿል
ቤጂንግ፤ በዩክሬን ሰላም እንዲመጣ ኪቭ እና ሞስኮን እያነጋገርኩ ነው ብላለች
አሜሪካ፤ የሩሲያ ቀንደኛ አጋር ናት ብላ የምትከሳት ቻይና በዩክሬን ሰላም እንዲመጣ ፍላጎቷ መሆኑን ገልጻለች።
ከአመት በፊት ከሩሲያ ጋር “ገደብ የለሽ” ግንኙነት ለመፍጠር የተስማማቸው ቻይና ሩሲያ በዩክሬን ላይ የጀመረችውን ወታደራዊ ዘመቻ ለማውገዝ ፈቃደኛ እንዳልሆነች ይታወቃል፡፡
- የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን የምእራባውያን ዋና አላማ "ሩሲያን መበታተን ነው” አሉ
- ሩሲያ ከአሜሪካ ጋር የነበራትን የኒውክሌር ስምምነት ብታቋርጥም ለህጉ እገዛለሁ አለች
ከቀናት በፊት በህንድ በተካሄደው የቡድን -20 ስብሰባ ላይ ከምዕራባውያኑ የተለየ አቋም ማራመዷም የሚታወስ ነው፡፡
ይሁን እንጅ ለጦርነቱ አሜሪካን እና አጋሮቿን ተጠያቂ የምትደርገው ቻይና፤ በዩክሬን ያለው ቀውስ በሰላም እንዲቋጭ ፍላጎት መሆኑ አስታውቃለች፡፡
ቤጂንግ ከተጀመረ ድፍን አንድ አመት ያስቆጠረውን የዩክሬን ጦርነት እንዲያበቃ ያስችላል ያለችውን ባለ 12 ነጥብ እቅድም ይፋ አድርጋለች፡፡
ቤጂንግ ባቀረበቸው ምክር ሃሳብ መሰረት ከሆነ በዩክሬን ምድር ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ ሩሲያ ጦሯን ማስወጣት አለባት፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ቻይና፤ ሰላም እንዲመጣ ኪቭን ጨምሮ በችግሩ ውስጥ ካሉ ሁሉንም ወገኖች ጋር ግንኙነት እንዳደረገች እና አቋሟ ግልጽ እንደሆነም ገልጻለች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ በቤጂንግ በሰጡት መግለጫ “ዋናው ሰላም ጥሪ ማቅረብ፣ ውይይትን ማሳደግ እና ለችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሄ ማበጀት ነው” ብለዋል።
የኔቶ አጋሮች ቻይና ሰው አልባ አውሮኘላኖችን ጨምሮ ወታደራዊ እርዳታ እንዳታቀረብ ለማሳመን እየሞከርን ነው ሲሉ እየተደመጡ ነው፡፡
የሲአይኤ ዳይሬክተር ዊሊያም በርንስ ፤ የአሜሪካ የስለላ ድርጅት እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ቤጂንግ ለሩሲያ ወታደራዊ ዕርዳታ ለማቅረብ እያሰበች እንደሆነ ያምናል ብለዋል ።
የአሜሪካ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን በበኩላቸው "ነገሮች በዚህ መንገድ ከቀጠሉ ቻይና ዋጋ ትከፍላለች" ሲሉ ለሲኤንኤን ተናግረዋል፡፡
የዩክሬን ጦርነት ጉዳይ አሁንም መፍትሄ ያልተበጀለት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የምእራባውያን ዋና አላማ " የቀድሞዋን የሶቪየት ህብረት እና ዋናውን ክፍል - የሩሲያ ፌዴሬሽን መበታተን ነው" ሲሉ እሁድ እለት ከሩሲያ-1 ቻናል ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
አሁንም ቢሆን አሜሪካ የሚዘወር ዓለም ሊኖር እንደማይችልም ነበር የተናገሩት ፑቲን፡፡
ፑቲን ይህን ይበሉ እንጅ ኔቶ እና ምዕራባውያን በተቃራኒ ጦርነቱን የተፈረካከሰቸውን ሩሲያ ለመመለስ የተደረገ ወረራ ነው ሲሉ ይገልጹታል፡፡