አሜሪካ በበኩሏ የአለም አቀፍ ህጉን ተከትዬ በታይዋን ሰርጥም ሆነ በኢንዶ ፓስፊክ ቀጠና ቅኝቴን እቀጥላለሁ የሚል ምላሽ ሰጥታለች
የአሜሪካ የስለላ አውሮፕላን በታይዋን ሰርጥ በኩል መብረሩ የቻይና ባለስልጣናትን ማስቆጣቱ ተነግሯል።
የቻይና “ምስራቃዊ ቲያትር” እዝ ቃል አቀባይ ኮሎኔል ሺ ይ ፥ ዋሽንግተን የቀጠናውን ውጥረት የሚያባብስ ድርጊቷን ገፍታበታለች ብለዋል።
የአሜሪካ ጄት በታይዋን ሰርጥ ያደረገው በረራ የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት የሚያናጋና ጸብ ጸጫሪ ድርጊት መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ግሎባል ታይምስ ይዞት የወጣው ዘገባ ዋሽንግተን ከመሰል ህገወጥ የሰለላ ድርጊቷ እንድትታቀብም ይጠይቃል።
አሜሪካ ግን በታይዋን ሰርጥም ሆነ በሌላ አለም አቀፍ ህጉ በሚፈቅድላት አካባቢ የቅኝት ስራዋን እንደምትቀጥል ነው ያስታወቀችው።
ዋሽንግተን እና ቤጂንግ መሰል መካሰስ ውስጥ ሲገቡ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
የሲ ኤን ኤን ጋዜጠኞችን የያዘች የአሜሪካ አውሮፕላንም ባለፈው አርብ በደቡብ ቻይና ባህር አቅራቢያ ፓራሴል ደሴቶች ስትደርስ በቻይና የጦር አውሮፕላኖች ወደመጣችበት እንድትመለስ መገደዷ ይታወሳል።
“አሜሪካ ከቻይና በሺዎች የሚቆጠር ኪሎሜትሮች ርቃ ብትገኝም ወደ ደቡብ የቻይና ባህር እና የታይዋን ሰርጥ በተደጋጋሚ የጦር መርከቦቿን እና አውሮፕላኖቿን ልካለች፤ ይህ ፍጹም ጸብ አጫሪነት ነው” ይላል የግሎባል ታይምስ ዘገባ።
24 ሚሊየን ህዝብ የሚኖርባት ታይዋን የሉአላዊ ግዛቴ አካል ናት የምትለው ቻይና በየቀኑ ወታደራዊ አውሮፕላኖቿን እና መርከቦቿን ወደ ታይዋን ሰርጥ ትልካለች።
በዛሬው እለትም 14 አውሮፕላኖች እና ሶስት መርከቦችን ወደ ደሴቷ አቅራቢያ ልካ ቅኝት ማድረጓን የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ቻይና ይህን ድርጊቷን እንደ ሉአላዊ መብቷ የምትቆጥረው ጉዳይ ቢሆንም ምዕራባውያን ግን በበጎ አይመለከቱትም።
የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር እና ወታደራዊ ሹማምንትም ቤጂንግ በታይዋን ላይ የሃይል እርምጃ በመውሰድ ለመጠቅለል እየተዘጋጀች ስለመሆኑ እየገለጹ ነው።
በፓስፊክ የአሜሪካ ጦር አዛዡ ጀነራል ቻርለስ ፍላይን፥ “ቻይና ጠንካራ ጦር ገንብታለች፤ በየቀኑ የሚያደርጉት ልምምድም ለአንድ ተልዕኮ ዝግጁ ሳይሆኑ እንደማይቀር ያሳያል” ብለዋል።
ጀነራሉ ቤጂንግ እየገነባቸው ያለው ጦር መከላከልን ኢላማ ያደረገ ብቻ እንዳልሆነና ባልተጠበቀ ጊዜ ወደማጥቃት ሊሸጋገር እንደሚችልም ነው ያሳሰቡት።
የአሜሪካ የሰለላ ድርጅት (ሲ አይ ኤ) ዳይሬክተሩ ዊሊያም በርንስም፥ ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ጦራቸው በ2027 በታይዋን ላይ ለሚፈጸም ወታደራዊ እርምጃ ዝግጁ እንዲሆን ማዘዛቸውን ደርሰንበታል ማለታቸው የሚታወስ ነው።