በየመን 150 ስደተኞችን የያዘ ጀልባ መስጠሙን ተከትሎ በርካቶች ሞተዋል ተብሎ ተሰግቷል
አይ.ኦ.ኤም የአደጋውን መጠን በተመለከተ እያጣራ መሆኑን ገልጿል
በመቶዎች የሚቆጠሩ የአፍሪካ ቀንድ ዜጎች ድንብር አሳብረው ወደ ሳዑዲ አረቢያና የመን እንደሚሰደዱ ይታወቃል
በየመን የጀልባ መስጠም አደጋ በርካታ ስደተኞች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ስጋት መኖሩ ተገለፀ፡፡
በየመን ጠረፍ አቅራቢያ አንድ ጀልባ መገልበጧን ተከትሎ በደርዘን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ስደተኞች ህይወታቸው ሳያልፍ አይቀርም ተብሎ ተሰግቷል፡፡
በየመን ላህጅ ግዛት የሚገኙ ዓሳ አጥማጆች በራስ አል-አራ አቅራቢያ ከሚገኘው ውሃ 25 አስከሬኖችን ማግኘታቸውን መግለፃቸውን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤ.ኤፍ.ፒ ዘግቧል ፡፡
ከ160 እስከ 200 የሚደርሱ ሰዎችን የያዘ ጀልባ ከሁለት ቀናት በፊት በአካባቢው መገልበጡንም ነው አንድ የግዛቱ ባለ ስልጣን የተናገሩት፡፡ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) የአደጋውን መጠን በተመለከተ እያጣራሁኝ ነው ብለዋል፡፡
"የአይ.ኦ.ኤም አባላት በአካባቢው በመኖራቸው የተረፉ ሰዎችን ፍላጎት ለማገዝ ዝግጁ ናቸው"ሲልም በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል።
አደን አል-ጋድ የተባለ አንድ የየመን የዜና ምንጭ በበኩሉ እስከ 150 የሚደርሱ ስደተኞች መስጠማቸውን ከምንጮቹ ማግኘቱን ጠቁሞ አራት የመናውያን እንደሚገኙበትም አስታውቋል።
ራስ አል-አራ የመን እና ጅቡቲን የሚለይ እና የቀይ ባህርን ከባህረ ሰላጤው ጋር የሚያገናኝ 20 ኪ.ሜ ስፋት ያለው ነው። ከባብ አል-ማንዳብ በስተምሥራቅ ያለው አካባቢ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የሚጠቀሙበት የባህር ዳርቻ ነው፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከአፍሪካ ቀንድ በተለይም ከኢትዮጵያና ሶማሊያ የመጡ ስደተኞች ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት መስመሩን አቋርጠው ወደ የመን ይሻገራሉ፡፡
ብዙዎቹ የህገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎቹ ጀልባዎች ከመጠን በላይ የተጨናነቁ እና ለውሃው ተስማሚ ያልሆኑ በመሆናቸው ጉዞው በአደጋ የተሞላ እንደሆነም እሙን ነው፡፡
ስድሰተኛ ዓመት ባስቆጠረ የእርስ በእርስ ጦርነት የምትታመሰው የመን የገቡ ብዙ ስደተኞች ቤተሰቦቻቸው እስኪከፍሉ ድረስ በህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች እጅ ለቀናት ወይም ለወራት ተይዘው ይቆያሉ፡፡
አይ.ኦ.ኤም እንዳለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ የመን የሚደርሱ የስደተኞች ቁጥር ዝቅ ብሏል። በዚህ ዓመት 5ሺ 100 ስደተኞቹ ሲገቡ እ.ኤ.አ በ2020 ቁጥሩ 35ሺ ንዲኁም በ 2019፤ 127ሺ ነበር፡፡
በሚያዝያ ወር በህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች የምትተዳደር ጀልባ ከየመን ወደ ጅቡቲ በመጓዝ ላይ ሳለች ተገልብጣ ቢያንስ 44 ስደተኞች መሞታቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡