በምስራቅ ወለጋ ዞን የተፈጸመው ግድያ እና መፈናቀል ጉዳይ
መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ያለው ነገር የለም
በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ግድያ ሽሽት ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላውንም ናዋሪዎች ተናግረዋል
በምስራቅ ወለጋ ዞን በተፈጸም ጥቃት በርካቶች በአስቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ነዋሪዎች ለአል ዐይን አማርኛ ተናገግረዋል።
ነዋሪዎቹ እንደገለጹት በተለይ በኪረሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ብሄራቸው እየተለየ ተገድለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችም ተጨማሪ እልቂትን ሽሽት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅተዋል፡፡
የሰሞኑ ግጭት መንስኤ በኪረሙ በእስራ ላይ የነበሩ የአማራ ተወላጆች ግድያ መሆኑን ከአንገር ጉቴ ሸሽተው ስቡንሱሬ ቀበሌ የሚገኙ ስማቸው እንዳይጠቅሰ የፈለጉ ነዋሪ ለአል አይን አማርኛ ተናግረዋል።
“የመንግስት አካላት ሸኔ ይገድላችኋል ኑ ወደ ካምፕ ግቡ በማለት የአማራ ገበሬዎችን ስብስበው ኪረሞ ማዘጋጃ ቤት ውስጥ አስረዋቸው ነበር፤ ሽማግሌዎች የታሰሩት እንዲፈቱ ጥረት ቢያደርጉም ኦሮሞዎች እየተለቀቁ አማራዎች ግን እንዳይወጡ ተደርጓል” የሚሉት አስተያየት ሰጪው የስሞኑ ችግር መንስኤም ከዚሁ ጋር ይያያዛል ብለዋል።
እኝህ ነዋሪ በእስራ ላይ የነበሩትን የአማራ ተወላጆች ጊዳ ወደተባለ ቦታ አግቶ ለመውሰድ የተደረገው ጥረትም የአማራ ተወላጆችን ከኦሮሚያ ልዩ ሃይል ጋር እንዲጋጩ ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡
ቅዳሜ ህዳር 24፣ 2015 ማለዳ ላይ የተጀመረው ጥቃትም ከ200 በላይ የአማራ ተወላጆችን ህይወት መቅጠፉንና በርካቶችም መቁሰላቸውን ተናግረዋል ነዋሪው።
“ከነቀምቴ በርካታ የኦሮሚያ የጸጥታ ሃይል ወደ ጉቴን እየመጣ ነው” መባሉም በከተማዋ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች የመኖሪያ ቤታቸውን ለቀው በጫካ ውስጥ እንዲደበቁ ምክንያት ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኪረሙን አሰቃቂ ጥቃት ተከትሎ “አማራው ለቆ ወደ ሃሮ፤ ኦሮሞው ደግሞ ወደ ጊዳ አያና ሸሽቷል” የሚሉት የአይን እማኙ፤ ህፃናት፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞች ህይወታችንን ለማትረፍ በመሰደዳቸው ጉትን ሰው አልባ ሆናለች ብለዋል።
ነዋሪው አንገር ጉቴ ላይ ብቻ 56 ሰዎች መቀበራቸውን እና በየጫካው የሟቾች ፍለጋው ስለቀጠለም ቁጥሩ ከፍ ሊል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው የአንገር ጉቴ ከተማ ነዋሪ በነበረው ችግር የኦሮሞ ተወላጆችም የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን ለአል አይን ገልጸዋል።
እስካሁን ሁለት ኦሮሞዎች መገደላቸውን አውቃለሁ የሚሉት የአይን እማኙ፣ ግድያን ሽሽት የአንገር ጉቴ ከተማ የኦሮሞ ተወላጆችም ወደ ነቀምትና ሌሎች አካባቢዎች ተፈናቅለው ከተማዋ ባዶ ሆናለች ብለዋል።
“ፋኖ ተደራጅቶ ሊወጋችሁ እየመጣ ነው” የሚል መረጃ መሰራጨቱም ህዝቡን ሽብር ውስጥ መክተቱን ገልጸዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች በጊዳ አያና ተፈናቅለው እንደሚገኙና ቀጣይ እጣ ፈንታቸውም አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል የአይን እማኙ።
ለሰሞኑ ጥቃት ተጠያቂው ማነው?
ለሰሞኑ ጥቃት የአማራ ተውላጆች የኦሮሚያ ልዩ ሃይልን፣ የኦሮሞ ተወላጆች ደግሞ የአማራ ታጣቂዎችን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
የአማራና የኦሮሞ ህዝብን እያራራቅ ያለው የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ነው የሚሉት በስልክ ያነጋገርናቸው የአንገር ጉቴ ከተማ ነዋሪ፥ የሰሞኑ ጥቃት ሸኔ ላይ ለማላከክ ጥረት ይደረጋል እንጂ ዋነኛ ተጠያቂው የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ነው ብለዋል።
“ሸኔ ከገበሬው አቅም አይበልጥም፤ ልዩ ሃይል ከሌለ ሸኔ የለም፤ ተዋልዶ ተዛምዶ የኖር ህዝብን እያባላ ያለው ልዩ ሃይሉ ነው” ብለዋል።
የኦሮሞ ተወላጁ የሆኑት የአንገር ጉቴ ነዋሪ ስር ያሲን “ሸኔ ወደ ጉትን አንድም ቀን መጥቶ አያውቅም ውጊያው በኦሮሚያ ልዩ ሃይልና በአማራ ታጣቂዎች መካከል ነው” ይላሉ።
ለሰሞኑ ጥቃት ግን የታጠቁና በብር የተገዙ “ፋኖዎች” ዋነኛ ተጠያቂዎች መሆናቸውን ይናገራሉ።
አንደር ጉቴ እና ጊዳ መካከል ያሉ የአማራ ታጣቂዎች ችግር መፍጠር ከጀመሩ ወራት መቆጠሩን በማንሳትም ህዝቡን እያማረሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ይህም የዜጎችን እንቅስቃሴ እና ደህንነት አደጋ ላይ መጣል በመጀመሩ ከኦሮሚያ የጸጥታ ሃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ ገብተዋል ይላሉ፡፡
የአማራ ተወላጁ ነዋሪ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም፤ “ስውን የሚገድልም ሆነ የሚዘርፍ የአማራ ሃይል በአካባቢው የለም፤ ሆን ተብሎ በአማራ ላይ የተከፈተ ዘመቻ ነው” ብለዋል።
የሰሞኑ ግጭትም አማራውን ትጥቅ ለማስፈታት የተያዘው እንቅስቃሴ አካል እንደሚሆን በማመን ጉዳዩ እልቂቱን እንዳያባብሰው ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ነዋሪው ለአል ዐይን አማርኛ እንተናገሩት አሁን ላይ መረጋጋት እየታየ ቢሆንም የቀጣይ ደህንነታቸው ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስትም አፋጣኝ መፍትሄን እንዲያበጅ ጠይቀዋል ነዋሪው፡፡
የፌዴራሉም ሆነ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እስካሁን ግድያውን በተመለከተ ያወጡት መግለጫ የለም።ከክልሉ መንግስት እና ከፌደራል መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡