በሶማሊያው የቅዳሜ ጠዋት የቦምብ ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 79 ደረሰ
በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ትናንት ታህሳስ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ሰዎች በሚበዙበት አካባቢ መኪና ላይ ተጠምዶ በፈነዳ ቦምብ 79 ሰዎች መሞታቸው ይፋ ሆኗል፡፡
በትንሹ 125 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና እየተከታተሉ እንደሚገኙ የአምቡላንስ አሽከርካሪዎችን ዋቢ አድርጎ ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
ጥቃቱን አስከፊ የሽብር ድርጊት ያሉት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሞሀመድ አብዱላሂ ሞሀመድ-ፎርማጆ ለጥቃቱ የአል-ቃኢዳውን ቡድን አል ሸባብን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
ከሟቾቹ መካከል አብዛኛው ፖሊሶች እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው ተብሏል፡፡
አል-ሸባብ ከዚህ ቀደምም በርካታ ጥቃቶችን በመፈጸም የሚታወቅ ሲሆን ከነዚህም ብዙዎች የተገደሉበት የኬንያው የትምህርት ቤቶች እና የገበያ ማዕከል ጥቃቶች ይጠቀሳሉ፡፡
ምንጭ፡-ሲጂቲኤን