የቀድሞው ኬንያዊ ሯጭ አበረታች መድኃኒት በመጠቀሙ ለ16 ወራት ታገደ
የቀድሞው ኬንያዊ ሯጭ አበረታች መድኃኒት በመጠቀሙ ለ16 ወራት ታገደ
የቀድሞው ኬንያዊ የግማሽ ማራቶን ሯጭ ሳሚ ኪትዋራ አበረታች መድኃኒት በመጠቀሙ ምክንያት ለ16 ወራት ከውድድር መታገዱን የአትሌቲክስ ኢንተግሪቲ ዩኒት (አኢዩ) በትናንትናው እለት አስታውቋል፡፡
ኪትዋራ የተከለከለውን ተርቡታላይን የተባለውን ዕፅ መጠቀሙ በምርመራ በመረጋገጡ መታገዱን አኢዩ ገልጿል፡፡
እገዳው ከባለፈው ሚያዚያ ጀምሮ የሚጸና ስለሆነ ከዚያ በኋላ በየትኛውም ውድድር ኪትዋራ ያስመዘገበው ውጤት ካለ እንዲሰረዝ ተወስኗል፡፡
አኢዩ እንደገለጸው ከሆነ ሯጩ ውሳኔው ላይ ይግባኝ ማለት ይችላል፡፡ ኪትዋራ ለመጀመሪያ ጊዜ የተወዳደረው እ.ኤ.አ በ2012 በችካጎ ማራቶን ሲሆን ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሎ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኪቲዋራ እ.ኤ.አ በ2009 የተካሄደው የሮተር ዳም ግማሽ ማራቶን አሸናፊ ነው፡፡
የ33አመቱ ኪትዋራ የአለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ያወጣውን የፀረ-አበረታች ህግ ከጣሱ ኬንያውያን መካከል የቅርቡ ሆኗል፡፡
በዚህ ወር መጀመሪያ ሌላኛው የኬንያ ሯጭ ፊሊፕ ኪሙታይ መታገዱ የሚታውስ ነው፡፡
የኬንያ የስፖርት ሚኒስቴር ወንጀል ሲሰሩ በተገኙ አትሌቶች ላይ እስርን ጨምር ቅጣት ለመጣል የሚያስችል ህግ ለማውጣት እንደሚሰራ ገልጾ ነበር፡፡